ጉግል ማፕስ ለሥነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ መስመሮችን ማሳየት ሊጀምር ነው

ጉግል ማፕስ ለሥነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ መስመሮችን ማሳየት ሊጀምር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጉግል ማፕስ አሽከርካሪዎችን በተቀመጡ መስፈርቶች መሰረት የበለጠ ተስማሚ ሥነ ምህዳር (ኢኮ ፍሬንድሊ) ባለው አካባቢ እንዲያሽከረክሩ ማመልከት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።

ይህ አቅጣጫ ጠቋሚ መተግበሪያ የትራፊክ እንቅስቃሴንና የመንገድ ሁኔታን ከግምት ውስጥ በማስገባት አነስተኛ የካርቦን ልቀት ጉዞ ማድረግ የሚቻልበትን መስመር ይጠቁማል።

ጉግል ይህ አሰራር በቅድሚያ በአሜሪካ ተግባራዊ እንደሚሆን ከዚያም በዓመቱ መጨረሻ አካባቢ ደግሞ "በመላው ዓለም ለማስፋት" እቅድ መኖሩን አስታውቋል።

ይህ አዲሱ አሰራር ጉግል የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ያለው ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ተብሏል።

መተግበሪያው ሥራውን ሲጀምር ተጠቃሚዎች ካልቀየሩት በስተቀር አማራጩ "ለሥነ ምሕዳር ተስማሚ" ላይ እንደሚሆን ተገልጿል።

ሌሎች ፈጣን መንገዶች በኖሩ ጊዜ ጉግል አማራጮችን አቅርቦ ተጠቃሚዎች አነስተኛ የካርበን ልቀት ያለበትን መስመር እንዲመርጡ ያደርጋል ተብሏል።

የጉግል ምርቶች ዳይሬክተር የሆኑት ራሰል ዲከር "ያየነው ነገር ለግማሽ ያህሉ መንገድ ለሥነ ምህዳር ተስማሚ የሆነ አማራጭ በዝቅተኛ ዋጋ ወይንም ያለምንም የዋጋ ለውጥ ማመልከት እንደምንችል ነው" ብለዋል።

ይህ አቅጣጫ መፈለጊያ መተግበሪያ ባለቤቱ አልፋቤት ሲሆን መተግበሪያው የካርበን ልቀትን የተለያዩ መኪናዎችን እንዲሁም መንገዶችን በመውሰድ እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት ብሔራዊ የኃይል ላብራቶሪ መረጃዎችን በመቀመር መፈተሹን ገልጿል።

"ይህ ሦስት ነገሮች በአንድነት ሲጣመሩ ጥሩ ማሳያ ነው መረጃ፣ ዘላቂነት እና የደንበኛ ምርጫ" ያለው ደግሞ የአማካሪ ድርጅቱ ኬይርኒ ባልደረባ ሲዳርት ፓታክ ነው።

"ለውሳኔ እየወላወሉ የነበሩትንም ከፍጥነት፣ ከአዋጭነት እና ከዋጋ አንጻር እንዲወስኑ ይረዳቸዋል" ሲል አክሏል።

ከሰኔ ወር ጀምሮ ጉግል አሽከርካሪዎችን አነስተኛ የካርበን ልቀት ባለበት መስመር እንዲያሽከረክሩ ማሳሰቢያ ይልክላቸዋል።

ይህ በጀርመን፣ በፈረንሳይ፣ በኔዘርላንድስ፣ በስፔን እና በዩናይትድ ኪንግደም የተለመደ አሰራር ነው።

"ከአምስተርዳም እስከ ጃካርታ ባሉ ከተሞች አነስተኛ የካርበን ልቀት ያላቸው ስፍራዎች ተለይተዋል። በእነዚህ አካባቢዎች አየሩ ንፁህ እንደሆነ እንዲቆይ በሚል የተወሰኑ የናፍጣ መኪኖች እንዳይንቀሳቀሱ ገደብ ተጥሎባቸዋል" ብሏል ጉግል።

"ያሉ ጥረቶችን ለማገዝ አሽከርካሪዎች በእነዚህ አካባቢዎች ሲነዱ የበለጠ ለማንቃት የሚያስችል ሥርዓት ላይ እየሰራን ነው።"

በዚህ ዓመት አዲሱ የጉግል ገጽታ ይፋ ሲደረግ የጉግል ማፕስ ተጠቃሚዎች በአንድ አካባቢ ከሚገኙ የመጓጓዣ አማራጮች (ባቡር፣ አውቶቡስ፣ ብስክሌት) መካከል በአንድ ስፍራ መምረጥ እንዲችሉ ይደረጋል ተብሏል።

ይህ ግዙፍ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የተፈጥሮ አካባቢ የሚጠቀምበትንና ከተሞች በ2030 የካርበን ልቀት ነጻ እንዲሆኑ እንደሚሰራ ቃል ገብቷል።