በሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች በተከሰተው ግጭት ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቀሉ

በጅሌ ድሙጋ የተፈናቀሉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Jile Dimuga Facebook page

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች ውስጥ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው የአካባቢው ባለስልጣናት ለቢቢሲ ገለፁ።

በሁለቱ አካባቢዎች ከሳምንት በፊት በተከሰተውና ለቀናት በቆየው ግጭት ከተፈናቀሉት ነዋሪዎች በተጨማሪ በርካታ ሰዎች መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን በንብረትም ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረ ጻዲቅ በተከሰተው ችግር ምክንያት በዞኑ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ41 ሺህ በላይ እንደሆኑ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በግጭቱ ምን ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ የተጠየቁት ኃላፊው "የሞቱ ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ የሚያጣራ ቡድን አዋቅረን መረጃ እየተሰበሰበ ነው" ብለዋል።

እስካሁን ድረስ እጃቸው ላይ የደረሰው መረጃ 41 ሺህ 625 ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የሚያሳይ መሆኑን የገልጹት አቶ ታደሰ፤ ነገር ግን ወደ ዘመድ አዝማድ እና ሌላ አካባቢ የሸሹ ስለሚኖሩ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል ሲሉ ይናገራሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ግጭቱ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ውስጥ የምትገኘዋ ጅሌ ድሙጋ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ጀማል ሐሰን በተፈጠረው ችግር ሳቢያ በወረዳቸው 40ሺህ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"እስካሁን እጃችን በደረሰው መረጃ መሰረት 67 ሰዎች መሞታቸውን፣ 114 መቁሰላቸውን እና በወረዳው ስምንት ቀበሌዎች 815 ቤቶች መቃጠላቸውን ለማወቅ ችለናል" ሲሉ የደረሰውን ጉዳት በአሃዝ አስቀምጠዋል።

ከዚህ ቀደም ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወደ ሆስፒታል ሲሄዱ ጥቃት ደርሶባቸው ስለነበር አብዛኞቹ ተጎጂዎች በቤታቸው ውስጥ መቅረታቸውን እና በቂ ሕክምና አለማግኘታቸውንም ጨምረው አስረድተዋል።

በጅሌ ድሙጋ ተፈናቅለው የሚገኙ ሰዎች ስላሉበት ሁኔታ የተጠየቁት አቶ ጀማል፣ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት የተደረገላቸው ድጋፍ እንደሌለ እና የተፈናቀለው ገበሬ እርስ በእርስ እየተረዳዳ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አክለውም የክልልም ሆነ የፌደራል አካላት ስለ አሉበት ሁኔታ ለመጠየቅ አለመምጣታቸውን ገልፀዋል።

በግጭቱ የተፈናቀሉት ሰዎች ትምህርት ቤቶች መስጂዶች እና በተለያዩ ቦታዎች ተበተትነው እንደሚገኙ አቶ ጀማል ይናገራሉ።

የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪውአቶ ታደሰ በበኩላቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ደብረብርሃን፣ አጣዬ፣ ኤፍራታ፣ ሸዋ ሮቢት ገንደ ውሃ፣ መሀል ሜዳ እና የተለያዩ ቦታዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።

አቶ ታደሰ አክለውም ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ በማዋቀር የተፈናቀሉ ሰዎች እርዳታ እንዲያገኙ እየሰራን ነው ይላሉ።

"ሸዋ ሮበት አጣዬ እና ኤፍራታ ከተሞች ውስጥ የምግብ ቁሳቁስ ከማቅረብ ጀምሮ ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ የማድረግ እንዲሁም ፀጥታውን የማስከበር ሥራዎችን እየሰራን ነው" ብለዋል።

አቶ ታደሰ አክለውም የፀጥታ ሁኔታውነ በማስመልከት በአጣዬ፣ በማጀቴ፣ እና በድሙጋ አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ እና ይህም ሕብረተሰቡን ስጋት ውስጥ መክተቱን ይናገራሉ።

አቶ ጀማልም የአቶ ታደሰን ሃሳብ አረጋግጠው የመከላከያ ሠራዊት ተኩስ ወደ ሚሰማባቸው አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ይፈልጋል የሚሉት አቶ ታደሰ ለዚህም ውይይትና መስማማት እንደሚያስልግ ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት አንድ ቡድን መላኩን ዞኑም ኮሚቴ ማዋቀሩን በመግለጽ እነዚህ ቡድኖች ግጭቱ ከተከሰተባቸው ሁለቱ ዞኖች ጋር በመሆን ችግሩን ይፈታሉ ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

በግጭቱ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ትራንስፖርት ወደ ሥራ ተመልሷል።