ኮሮናቫይረስ፡ እንግሊዝ ኬኒያን ጨምሮ የሦስት አገራትን መንገደኞችን ልታግድ ነው

አንዲት መንገደኛ አውሮፕላን ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የእንግሊዝ መንግሥት በኮሮረናቫይረስ ስጋት ምክንያት ከኬንያ፣ ከፊሊፒንስ፣ ከባንግላዲሽና ከፓኪስታን የሚነሱ መንገደኞች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ወደ አገሩ እንዳይገቡ እገዳ መጣሉን አስታወቀ።

አገራቱ የተካተቱበት 'ቀይ መዝገብ' ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎች አገራት የሚመጡ መንገደኞች ወደ እንግሊዝ እንዳይገቡ የሚከለክል እገዳ ነው።

ከሚቀጥለው ሐሙስ ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆነው በዚህ ዕገዳ ወደ ተዘረዘሩት አገራት ላለፉት 10 ቀናት የተጓዘ ወይም በአገራቱ በትራንዚት ያለፈ ዓለም አቀፍ መንገደኛ የእንግሊዝን መሬት እንዲረግጥ አይፈቀድለትም።

ይህ ዕገዳ የብሪታኒያና የአየርላንድ ፓስፓርት የላቸውን እንዲሁም የዩናይትድ ኪንግደም የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸውን መንገደኞች አይመለከትም።

ሆኖም ግን ተጓዦቹ ወደ አገር ሲገባ የእንግሊዝ መንግሥት ፍቃድ በሰጣቸው ለለይቶ ማቆያነት በተዘጋጁ ሆቴሎች ውስጥ ለ10 ቀናት የመቆየት ግዴታ ይኖርባቸዋል። ክፍያውንም ቀድመው ይፈፅማሉ።

እነዚህ መንገደኞች ሁለት የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማረጋገጫ ማምጣትም ይጠበቅባቸዋል። ይህ ማለት ግን በለይቶ ማቆያ የሚኖራቸው ጊዜ ያጥራል ማለት እንዳልሆነም ተመላክቷል።

የአገሪቱ የትራንስፖርት መስሪያ ቤት እንዳስታወቀው የጉዞ ዕገዳው ዋነኛ ዓላማ አዲሱን የኮሮናቫይረስ ዝርያ ስርጭትን መግታት ነው።

በተለይም በእንግሊዝ የደቡብ አፍሪካው አይነት የቫይረሱ ዝርያ የተገኘባቸው አብዛኞቹ ሰዎች ዓለም አቀፍ በረራ ከተጠቀሙ ጥቂት የአውሮፓ መንገደኞች ጋር የተያያዙ መሆኑንም መስሪያ ቤቱ ጠቁሟል።

ከየትኞቹ አገራት በቀዩ መዝገብ ውስጥ አሉ?

እሳካሁን ኢትዮጵያን ጨምሮ 40 የሚጠጉ አገራት መንገደኞች በዩናይትድ ኪንግደም መንግጅት 'ቀይ መዝገብ' ውስጥ ሰፍረዋል።

ከአፍሪካ፤ ኢትዮጵያ፣ አንጎላ፣ ቦትስዋና፣ ቡሩንዲ፣ ኬፕቨርዴ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ኢስዋቲኒ፣ ኬንያ፣ ሌሶቶ፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ሩዋንዳ፣ ሲሸልስ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያና ዚምባብዌ ይገኙበታል።

መካከለኛው ምሥራቅ ደግሞ ኦማን፣ ኳታርና ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ የሚገኙበት ሲሆን ከእስያ ባንግላዲሽ፣ ፊሊፒንስና ፓኪስታን አሉበት።

ከደቡብ አሜሪካ፤ አርጀንቲና፣ ቦሊቪያ፣ ብራዚል፣ ቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ ኢኳዶር፣ የፈረንሳይ ጉያና፣ ጉያና ፣ ፓናማ ፣ ፓራጓይ፣ ፔሩ፣ ሱሪናም፣ ኡራጓይና ቬኔዝዌላ ይገኛሉ።