የቡድን 7 አባላት በትግራይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች 'በእጅጉ ያሳስበናል' አሉ

ያለተገደበ አስቸኳይ የእርዳታ አቅርቦት እንዲመቻች ጠይቀዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ያለተገደበ አስቸኳይ የእርዳታ አቅርቦት እንዲመቻች ጠይቀዋል

ቡድን ሰባት (ጂ7) የሚባሉት የዓለማችን የኢኮኖሚ ኃያል አገራት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ግጭት ውስጥ የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በሚመለከት የሚወጡ ሪፖርቶች "በእጅጉ እንዳሳሰበቸው" ገለጹ።

ይህ ቡድን ሰባት የሚባለው የአገራት ስብስብ ዩናይትድ ኪንግደምን፣ አሜሪካንን እና የአውሮፓ ሕብረት ያሉበት ሲሆን በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ እየተዘገቡ ያሉትን ወንጀሎች በተመለከተ ምርመራ እንዲደረግና አጥፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል።

ጨምረውም ትግራይ ውስጥ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን ሆነው እየተዋጉ ይገኛሉ ያሏቸውን ወታደሮቿን ኤርትራ እንድታስወጣ ጠይቋል።

የሁለቱም አገራት ወታደሮች በግጭቱ ውስጥ ተፈጽመዋል በተባሉ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይከሰሳሉ።

የቡድን ሰባት አገራት በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ መውጣትን በተመለከተ ያስታወቁትን ውሳኔ እንደሚቀበለው ገልጿል።

ይህም ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ የጅምላ ግድያዎችን፣ ወሲባዊ ጥቃቶችን፣ ዘረፋና ስደተኞችን መጎሳቆልን የሚጨምር ነው። የቢቢሲ 'አፍሪካ አይ' ምርመራ 15 ሰዎች በኢትዮጵያ ወታደሮች መገደላቸውን የሚያመለክት መረጃን ማውጣቱ ይታወሳል።

የህወሓት ኃይሎች ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ ነበር ግጭቱ የተጀመረው።

በዚህ ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች የሞቱ ሲሆን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ተፈናቅለዋል።

በግጭቱ ውስጥ የህወሓት ኃይሎችም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመፈጸም ይከሰሳሉ።

የቡድን ሰባት አባል አገራት ባወጡት መግለጫ ላይ "በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችን፣ ጾታዊ ጥቃቶችን፣ ኢላማ ያልለየ የከባድ መሳሪያ ድብደባዎችና ነዋሪዎችንና ኤርትራውያን ስደተኞችን በኃይል ማፈናቀልን እናወግዛለን" ብለዋል።

"ተፈጸሙ በተባሉት ወንጀሎች ላይ ግልጽና ገለልተኛ ምርመራ ተደርጎ የሰብአዊ መብት ጥሰቶቹ ፈጻሚዎች ተጠያቂ ማድረግ አስፈላጊ ነው" በማለት አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡ በአገሪቱ ፓርላማ ውስጥ ባደረጉት ንግግር በትግራይ ክልል ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች እንዳሉ ተናግረው፤ መንግሥታቸው አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ አጥፊዎችን ተጠያቂ እንደሚያደረግ መግለጻቸው ይታወሳል።

በቡድኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና በአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ተወካይ የወጣው መግለጫ ጨምሮም በግጭቱ አካባቢ "እየተባባሰ ያለ የምግብ ዋስትና ችግር" እንደሚያሳስባቸው በመግለጽ "አስቸኳይና ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት" እንዲመቻች ጠይቋል።

በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከ70ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን መሰደዳቸውን የእርዳታ ድርጅቶች ይናገራሉ።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚለው አስካሁን ድረስ ከሁለት ሚሊዮን ሰዎች በላይ ሰዎች በክልሉ ውስጥ የተፈናቀሉ ሲሆን፤ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ የሰብዓዊ እርዳታ ይፈልጋሉ።