በትግራይ ስለተፈጸመው ግድያ በሚያሳየው ቪዲዮ ላይ የተደረገው ምርመራ ምን ያሳያል?

በትግራይ ስለተፈጸመው ግድያ በሚያሳየው ቪዲዮ ላይ የተደረገው ምርመራ ምን ያሳያል?

የቢቢሲ 'አፍሪካ አይ' ፕሮግራም ባደረገው ምርመራ በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጸመ አንድ ጭፍጨፋ በኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት መፈጸሙን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች አግኝቷል። በዚህም ቢያንስ 15 ወንዶች የተገደሉበትን ትክክለኛውን ቦታ ለመለየት ችሏል።

የታጠቁና የወታደር የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ያልታጠቁ ወንዶችን ከአንድ የገደል አፋፍ ላይ በመውሰድ አንዳንዶቹን ላይ በቅርብ ርቀት በመተኮስ አስከሬኖችን ወደ ገደል ገፍተው ሲጨምሩ የሚያሳይ ቪዲዮ በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታይቶ ነበር።

ቢቢሲ ይህ ድርጊት የተፈጸመው የኢትዮጵያ ሠራዊት የህወሓት ኃይሎችን እየተዋጋ ባለበት ትግራይ ክልል ውስጥ ማኅበረ ዴጎ ከተባለች ከተማ አቅራቢያ መሆኑን አረጋግጧል።

ቢቢሲ ያገኛቸውን ማስረጃዎች ለኢትዮጵያ መንግሥት በማቅረብ ምላሽ የጠየቀ ሲሆን መንግሥት "በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ነገሮችና ክሶች እንደ ማስረጃ ሊወሰዱ አይችሉም" በማለት "ገለልተኛ ምርመራዎችን ለማካሄድ የትግራይ ክልል ክፍት ነው" ሲል መልሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው እንደተናገሩት፣ ትግራይ ውስጥ በኢትዮጵያ ሠራዊት ተፈጸሙ ስለተባሉት ጥፋቶች አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ አጥፊዎች በሕግ እንደሚጠየቁ መናገራቸው ይታወሳል።