የምርጫ ቦርድ ውሳኔን በመቃወም ክስ የመሰረቱ ፓርቲዎች ምን ተወሰነላቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተገቢውን መስፈርት አላሟሉም በማለት ከሰረዛቸው ፓርቲዎች መካከል በሁለቱ ላይ የተላለፈው ውሳኔ እንዲነሳ ፍርድ ቤት ወሰነ።
ቦርዱን ውሳኔን በመቃወም ጉዳዩን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ካመለከቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ሕብረት እና የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር ምርጫ ቦርድ እንዲሰረዙ ያስተላለፈውን ውሳኔ መሻሩን ገልፀዋል።
ምርጫ ቦርድ ታኅሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ከ35 በመቶ በታች የሆኑ ትክክለኛ ፊርማ ያመጡ እና የተለያዩ በቦርዱ የተጠየቁትን መስፈርት ያላሟሉ ፓርቲዎች በማለት ከሰረዛቸው 26 ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ሕብረት እና የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር ይገኙበታል።
እነዚህ ፓርቲዎች ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ የምርጫ ጉዳይ ችሎት ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት፣ ችሎቱ ፓርቲዎቹ እንዲሰረዙ ተወስኖ የነበረው በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 9 (4) መሰረት መሻሩን አስታውቋል።
ችሎቱ አክሎም ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎቹን ለመሰረዝ ምክንያት ባደረገው ጉዳይ ላይ ፓርቲዎቹ መከላከያቸውን አቅርበው ምርጫ ቦርድ የመጨረሻ ውሳኔውን እንደሚያሳውቅ ገልጿል።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተቀመጠውን መስፈርት አሟልተው የተመዘገቡ እና ፈቃዳቸው የታደሰላቸው 33 ክልላዊ ፓርቲዎችና 20 አገር አቀፍ ፓርቲዎች ናቸው።
ከእነዚህ መካከል በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ 47 ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን አስመዝግበዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የምርጫ ጉዳይ ሁለተኛ ችሎት ጥር 16/2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት መሰረት የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር እንዲሰረዝ ምርጫ ቦርድ ያስተላለፈውን ውሳኔ ውድቅ ከማድረጉ በተጨማሪ፤ ፓርቲው መጀመሪያ የተሰረዘበት የመስራች አባላት ፊርማ አለማሟላት ጉዳይ ላይ መከላከያውን ካቀረበ በኋላ ቦርዱ ውሳኔ እንዲሰጥበት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በተመሳሳይ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ሕብረት ለፍርድ ቤት ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቶ የምርጫ ቦርድ ውሳኔን እየጠበቀ መሆኑን ፓርቲው ለቢቢሲ ተናግሯል።
የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር - የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 4 በመቶ ያገኘ መሆኑ በወቅቱ በምርጫ ቦርድ የተገለፀ ሲሆን፤ የመስራች ፊርማ ናሙና ማረጋገጫ ከ35 በመቶ በታች በመሆኑ እና የ1,142 መሥራች አባላት የነዋሪነት ማረጋገጫ አይነት ስላልተሟላ መሰረዙ ተገልፆ ነበር።
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ሕብረት ደግሞ የመሥራች አባላት ናሙናን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ 18 በመቶ ማግኘቱ በወቅቱ ይፋ የሆነው መረጃ ያሳያል።
የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ምን ነበር?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ታኅሣሥ 13/2013 ዓ.ም የመስራቾችን ፊርማ ማጣራት አካሂዶ 26 የፖለቲካ ፓርቲዎችን መሰረዙን አስታውቆ ነበር።
ከተሰረዙት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው እና ዘንድሮ በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ በኦሮሚያ ክልል ለመወዳደር በዝግጅት ላይ የነበረው የኦሮሞ ነጻነት አንድነት ግንባር ፓርቲ ይገኝበታል።
የፓርቲው ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ኡመር መሐመድ ለቢቢሲ "ከ400 ሺህ በላይ ሰዎችን ፊርማ በማሰባሰብ በተባለው ጊዜ አስገብተን ነበር" ሲሉ ተናግረዋል።
"ከዚያም በኋላ በምርጫ ላይ ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ እያለን ድርጅታችሁ ተሰርዟል ተባልን" በማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ላይ ታኅሣሥ 13/2013 ዓ.ም ባሰፈረው መግለጫ መሰረት በፓርቲው አባላት የፊርማ ናሙና ላይ ባደረገው ማጣራት 4 በመቶው ብቻ ትክክል መሆኑን ገልጾ ነበር።
አቶ ኡመር በበኩላቸው "ምርጫ ቦርድ ይህን ውሳኔ ዳግም እንዲያየው ብንጠይቅም መልስ አላገኘንም" ያሉት ሊቀመንበሩ "ግልባጭ እንዲሰጠን ብንጠይቅ አልተሰጠንም፤ ከዚያ በኋላ በተጻፈልን ደብዳቤ ብቻ ነው ፍርድ ቤት ጥያቄያችንን ያቀረብነው" ብለዋል።
የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ሕብረት ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ሱልጣን ቃሲም በበኩላቸው "በጋራ በመሆን አቤቱታ አቅርበን [ለፍርድ ቤቱ] የነበርን የኦሮሞ ፓርቲዎች ስድስት ነበርን፤ ይሁን እንጂ ለብቻ ለብቻ አቅርቡ ስለተባልን በግል አቅርበናል" ይላሉ።
በፓለቲካ ፓርቲ ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ሥርዓት ድንጋጌ 1162/2011 አንቀጽ 94/4 ላይ በተቀመጠው መሰረት አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በተለያየ ምክንያቶች በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከተሰረዘ እና በመሰረዙ ላይ ቅሬታ ካለው የቦርዱ ውሳኔ ፓርቲው ከደረሰው በኋላ በ30 ቀናት ውስጥ አቤቱታውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል ሲል ይገልጻል።
ከዚህም በተጨማሪ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከመሰረዙ በፊት ፓርቲዎች እንዲከላከሉ እድል መስጠት እንዳለበትም ይደነግጋል።
ይኹን እንጂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲከላከሉ እድል ሳይሰጣቸው መሰረዙን የኦሮሞ ነጻነት አንድነት ግንባር ሊቀመንበር አቶ ኡመር መሐመድ ይገልጻሉ።
የምርጫ ቦርድ ውሳኔን አስመልከተው ሲናገሩ፣ ፓርቲያቸው የሕግ ሂደትን አላሟላም መባሉን በተለይም፣ "የመስራች አባላት ፊርማ አላሟላም፤ አጣርተን ይህንኑ ስላረጋገጥን ከምዝገባ ሂደት ላይ ሰርዘናችኋል የሚል ውሳኔ ተላልፏል" መባላቸውን ይገልጻሉ።
"ይህ ውሳኔ መስተካከል አለበት ብለን ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ ብናቀርብም መልስ አልተሰጠንም። ከዚያ በኋላ ነው ወደ ፍርድ ቤት የሄድነው" የሚሉት ደግሞ የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ሕብረት ሊቀመንበር አቶ ሱልጣን ቃሲም ናቸው።
እነዚህ ሁለቱ ፓርቲዎች ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ፓርቲዎቹ እንዲሰረዙ ቦርዱ ያስተላለፈው ውሳኔ ውድቅ እንዲሆን ተደርጓል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ የምርጫ ጉዳይ ችሎት ጥር 16/2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት መሰረት የኦሮሞ ነጻነት አንድነት ግንባር እንዲሰረዝ ምርጫ ቦርድ ያስተላለፈውን ውሳኔ ውድቅ ከማድረጉ በተጨማሪ ፓርቲው መጀመሪያ የተሰረዘበት ምክንያት የመስራች አባላት ፊርማ ጉዳይ ላይ መከላከያውን ካቀረበ በኋላ ቦርዱ ውሳኔ እንዲሰጥበት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ፓርቲዎቹ በምርጫ ይሳተፉ ይሆን?
ፓርቲያቸው ላይ "ከሕግ ውጪ ተፅዕኖ ገጥሞናል" የሚሉት የኦሮሞ ነጻነት አንድነት ግንባር መሪ አቶ ዑመር መሐመድ ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በቀሩት ሁለት ወራት ውስጥ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል።
"ለምርጫ ቦርድ የፍርድ ቤት ውሳኔ ግልባጭና ማመልከቻ አስገብተናል፤ ከምርጫ ሂደት ወደ ኋላ ስለቀረን ሁኔታዎችን አመቻችተውልን ወደ ምርጫ ለመግባት ፍላጎት ስላለን በፍጥነት ውሳኔ እንዲሰጡን አቤቱታ አቅርበናል" በማለት የምርጫ ቦርድ ውሳኔን እየተጠባበቁ መሆኑን ይናገራሉ።
አቤቱታቸውንም ለምርጫ ቦርድ ካስገቡ አንድ ሳምነት እንደሆናቸውም ጨምረው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ሕብረት ሊቀመንበር አቶ ሱልጣን ቃሲም የምዝገባቸው ሂደት እንዲጠናቀቅ በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።
"በአሁኑ ሰዓት እንደ ቁልፍ ነገር አድርገን እየሰራን ያለነው ፈቃዳችንን ማግኘት ነው፤ ተመዝግበን ሕጋዊነታችን ከተረጋገጠ በኋላ ምርጫ ላይ መሳተፍ እና አለመሳተፋችንን ከአባላቶቻችን ጋር ተነጋግረን የምንወስነው ይሆናል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ዕጩዎችን መዝግቦ ማጠናቀቁን መግለፁ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት 47 ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ሲያስመዘግቡ፣ በግል ለመወዳደር ደግሞ 125 ዕጩዎች መመዝገባቸውን ቦርዱ ይፋ ያደረገው መረጃ ኣሳያል።
ዕጩዎቻቸውን ካስመዘገቡ ፓርቲዎች መካከል አርባ አንዱ ፌደራልና ለክልል ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ ሲሆን አራቱ ለክልል ምክር ቤት እንዲሁም የቀሩት ሁለት ፓርቲዎች ደግሞ ለተወካዮች ምክር ቤት ብቻ የሚወዳደሩ ናቸው።