በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ካፒቶል ሂል በደረሰ ጥቃት አንድ ፖሊስ ተገደለ

ለደህንነት መከላከያ ከተቀመጠ ግንብ ጋር የተጋጨች መኪና

የፎቶው ባለመብት, EPA

በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ካፒቶል ሕንጻ ላይ በደረሰ ጥቃት አንድ የፖሊስ ባልደረባ ሲሞት ሌላ ደግሞ ጉዳት ደርሶበት ሆስፒታል መግባቱ ተሰምቷል።

ፖሊስ የተፈጠረውን ሲያስረዳ አንድ መኪና ወደ ሕንጻው በመምጣት ለመከላከያ ከተቀመጠው ግንብ ጋር የተጋጨ ሲሆን ከመኪናው ውስጥ ቢላዋ የያዘ ሰው ወጥቶ ፖሊሱ ላይ ጥቃት ፈጽሟል።

ከዚህ በኋላ ሌላ ፖሊስ በከፈተው ተኩስ ተጠርጣሪው መሞቱ ታውቋል።

የደኅንነት ባለሥልጣናት ይህ ጥቃት ከሽብር ድርጊት ጋር አይያያዝም ሲሉ ተናግረዋል።

ከሦስት ወር በፊት ጥር ላይ በካፒቶል ሒል ሕንጻ ላይ የወቅቱ ፕሬዝዳነት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች አመጽ ቀስቅሰው ጥቃት ማድረሳቸው ይታወሳል።

የዋሺንግተን ዲሲ ሜትሮፖሊታን ፖሊስ ተጠባባቂ ኃላፊ ሮበርት ኮንቴ "ጥቃቱ በሕግ አስከባሪ አካላት ላይ ቢሆንም ወይንም በሌላ ላይ፣ ጉዳዩን ከስር መሰረቱ ለይቶ የማወቅ ኃላፊነት አለብን፤ ያንን እናደርጋለን" ብለዋል።

የካፒቶል ሂል ተጠባባቂ የፖሊስ ኃላፊ የሆኑት ዩጋናዳ ፒትማን ደግሞ "በጣም በጣም እያዘንኩኝ አንዱ ባልደረባችን በደረሰበት ጉዳት የተነሳ ሕይወቱ አልፏል" ብለዋል።

በደረሰበት ጥቃት የሞተው የፖሊስ ባልደረባ ዊሊያም ኢቫንስ የሚባል ሲሆን የካፒቶል ሂል ፖሊስ ሆኖ ላለፉት 18 ዓመታት ማገልገሉ ታውቋል።

"ኦፊሰር ኢቫንስ እና ቤተሰቡን በፀሎታችሁ አስቧቸው" ሲሉ ኃላፊዋ ጠይቀዋል።

የተፈፀመውን ጥቃት እየመረመሩ ከሚገኙ ግለሰቦች መካከል ሁለቱ ለሲቢኤስ በሰጡት መረጃ ጥቃቱን በማድረስ የተጠረጠረው የኢንዲያና ነዋሪ የሆነው የ25 ዓመቱ ወጣት ኖሃ ግሪን ነው።

የፎቶው ባለመብት, US Capitol Police

ፖሊስ በመዝገቡ ላይ ስለ ኖሃ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌለው ገልጿል።

በመጋቢት ወር አጋማሽ ላይ ኖሃ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ሥራውን መልቀቁን ያሰፈረ ቢሆንም በኋላ ላይ ሰርዞታል።

"በከፊል ከህመም ጋር በተያያዘ፤ ነገር ግን በዋናነት የሕይወት መንፈሳዊ ጉዞ " ነው ብሎ ነበር በዚህ የፌስቡክ መልዕክቱ ላይ የሥራውን የለቀቀበትን ምክንያት ያሰፈረው።

ኖሃ "ባለማወቅ እየወስድኩት በነበረው ዕፅ በደረሰብኝ የጎንዮሽ ጉዳት" በማለት እየተሰቃየ እንደነበር አስፍሯል።

ኖሃ በፌስቡክ ገፁ ላይ 'ኔሽን ኢስላም' በተሰኘ የጥቁር ብሔርተኞች የሐይማኖት ተቋም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳሳደረበት ጽፏል።

የፌስቡክ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ገፁ የግሪን መሆኑን አረጋግጠዋል።

ኩባንያው አክሎም "ከዚህ አሳዛኝ አደጋ በኋላ ሃሳባችን ሁሉ በካፒቶል የተገደለው የፖሊስ ባልደረባ እና ቤተሰቡ ጋር ነው" ብሏል።

ፌስቡክ የግለሰቡን አካውንት ከፌስቡክ እና ከኢንስታግራም ላይ ማጥፋቱን ገልጾ ጥቃቱን የሚያንቆለጳጵስ፣ የሚደግፍ ወይንም ተያያዥ የሆኑ መልዕክቶችን እንደሚሰርዝ አስታውቋል።

አክሎም "ጥቀቱ ላይ ምርመራ እያደረጉ ከሚገኙ ባለሙያዎች ጋረ እየሰራን ነው" ብሏል።

በአሁኑ ሰዓት የአሜሪካ ኮንግረስ መቀመጫ በሆነው በካፒቶል ሕንጻ አካባቢ የተጠናከረ ጥበቃ እየተደረገ ይገኛል።

የኮንግረስ አባላት በአሁኑ ሰዓት እረፍት ላይ በመሆናቸው አብዛኞቹ ፖለቲከኞች ጥቃቱ በተፈፀመበት ወቅት በሕንጻው ውስጥ አልነበሩም።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጥቃቱ ማዘናቸውን ገልፀው፤ ለፖሊስ ባልደረባው ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።

አክለውም በዋይት ሐውስ ባንዲራ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ማዘዛቸውን ገልፀዋል።

ናንሲ ፔሎሲ በበኩላቸው የፖሊስ ባልደረባውን "የዲሞክራሲያችን መስዋዕት" ሲሉ ገልፀውታል።

እንዲሁም ቸክ ሹመርና ሚች ማንኮኔል ሐዘናቸውን ከገለፁ መካከል ይገኙበታል።