የድምጻዊ አቤል ተስፋዬ እርዳታ ለ2 ሚሊዮን ዜጎች ምግብ ማቅረብ ያስችላል- የዓለም ምግብ ፕሮግራም

ዘ ዌኬንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ [ዘ ዊኬንድ] የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ሥራ ለመደገፍ የአንድ ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ለገሰ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በበኩሉ ድምጻዊ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲ እና ፕሮዲውሰር አቤል ተስፋዬ፣ በመድረክ ስሙ "ዘ ዌኬንድ" 1 ሚሊዮን ዶላር እንደሰጠው አስታውቋል።

ድምጻዊው በይፋዊ የትዊተር ገፁ ላይ ባሰፈረው መልዕክት "በኢትዮጵያ ከጨቅላ ሕጻናት እስከ አዛውንቶች በጭካኔ ሲገደሉ እና ከፍርሃት የተነሳ ቤታቸውን ጥለው ሲፈናቀሉ ስሰማ ልቤ ይሰበራል" ብሏል።

ድምጻዊው አክሎም ለእነዚህ ዜጎች የዓለም ምግብ ፕሮግራም 2 ሚሊዮን ምግብ ማቅረብ የሚያስችለው የ1 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።

ድምጻዊው አክሎም ሌሎች ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

ከኢትዮጵያዊ ቤተሰቦች በካናዳ ተወልዶ ያደገው ዘ ዊኬንድ (አቤል ተስፋዬ) በቅርቡ በሙዚቃው ስፍራ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ኤምቲቪ፣ ቪኤምኤና የአሜሪካ የሙዚቃ ሽልማቶችን አግኝቷል።

በየካቲት ወርም በአሜሪካውያን ዘንድ ከፍተኛ ስፍራ በሚሰጠው ሱፐር ቦውል የእግር ኳስ ጨዋታ በእረፍት ሰዓት ላይ በመዝፈን አድናቆት ተቸሮታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከድምጻዊው ያገኘውን ስጦታ በትግራይ ክልል በግጭቱ ምክንያት ተፈናቅለው እርዳታ ለሚጠብቁ ዜጎች እንደሚያውለው ገልጿል።

ድርጅቱ አክሎም ይህ ድጋፍ የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 2 ሚሊዮን ዜጎች በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ምግብ ለማቅረብ እንደሚረዳው ተናግሯል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እስካሁን ድረስ በትግራይ ለተፈናቀሉ 60 ሺህ ዜጎች በቆሎ፣ ሩዝ፣ ዘይት እያቀረበ መሆኑን ገልጿል።

አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ከማድረግ ባሻገር ድርጅቱ ለህጻናት፣ ለነፍሰጡር እና ለሚያጠቡ እናቶች የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት እያዳረሰ መሆኑን ገልጿል።

"ትግራይ ስላለው የምግብ ዋስትና ጉዳይ በእጅጉ ያሳስበናል" ያሉት የዓለም ፕሮግራም ፕሬዝዳንት ባሮን ሴጋር ናቸው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ 4.5 ሚሊዮን ዜጎች የአስቸኳይ ምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጾ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለ1.4 ሚሊዮን ያህሉ እርዳታ እንዲያቀርብ መጠየቁን ድርጅቱ አስታውቋል።

በትግራይ ክልል በጥቅምት 24 2013 ዓ.ም የተቀሰቀሰው ግጭት ከሰብል መሰብሰቢያ ወቅት ጋር መግጠሙ ሁኔታዎችን የበለጠ ውስብስብ ማድረጉን ድርጅቱ ገልጿል።