ኬንያ በዩናይትድ ኪንግደም ተጓዦች ላይ የአጸፋ ዕገዳ ጣለች

ሂትሮው አየር ማረፊያ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ኬንያ በዩናይትድ ኪንግደም የኮሮናቫይረስ የጉዞ ክልከላ 'ቀይ መዝገብ' ስር መካተቷን በመቃወም በበኩሏ አጸፋዊ እርምጃ ወሰደች።

ዩናይትድ ኪንግደም ከኬንያ የሚነሱ ሰዎችና በኬንያ በኩል የሚያልፉ መንገደኞች ወደ ግዛቷ እገዳ መጣሏን ተከትሎ በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ከዩናይት ኪንግደም ወደ አገሯ የሚገቡ ተጓዦች ለሁለት ሳምንታት በአስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩና ሁለት ጊዜ የኮቪድ-19 ምርመራ እንዲያደርጉ አስገድዳለች።

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዩናይትድ ኪንግደምን ውሳኔ ተከትሎ መግለጫ ባወጣው መግለጫ ኬንያ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገች ባለበት ወቅት በተወሰደው እርምጃ ማዘኑን ገልጿል።

ዩናይትድ ኪንግደም በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ኬንያን ጨምሮ ከፊሊፒንስ፣ ከባንግላዲሽና ከፓኪስታን የሚነሱ መንገደኞች ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ወደ አገሯ እንዳይገቡ እገዳ መጣሏን ያስታወቀችው ባለፈው አርብ ነበር።

እንዲህ አይነቱን እገዳ የጣለችባቸው የዓለም አገራት ከ30 በላይ ሲሆኑ ከጥቂት ሳምንታት በፊትም 'ቀይ መዝገብ' ከተባለው እዚህ ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያም መግባቷ ይታወሳል።

በእርምጃው የተቆጣችው ኬንያ ከመጪው አርብ ጀምሮ ወደ ናይሮቢ የሚገቡ የዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪዎችና ጎብኚዎች ለ14 ቀናት ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ይገደዳሉ።

በውሳኔው መሠረትም ተጓዦቹ በመንግሥት በተለየ ማቆያ ውስጥ የሚጠበቅባቸው እንዲሁም ሁለት ጊዜ ለሚያደርጉት የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሙሉ ወጪያቸውን በእራሳቸው እንዲሸፍኑ ይገደዳሉ ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ።

ነገር ግን ከዩናይትድ ኪንግደምም ሆነ በአገሪቱ በኩል አቋርጠው የሚመጡ ኬንያውያን ይህ ውሳኔ አይመለከታቸውም ተብሏል።

ኬንያ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላት አስታውሶ በወሰደችው በዚህ እርምጃ ማዘኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ገልጾ፤ ውሳኔው "የተወሰኑ አገራትና ሕዝቦችን" የለየ ነው ሲል ወቅሷል።

በዩናይትድ ኪንግደም ውሳኔ መሠረት ከቅዳሜ ጀምሮ ከኬንያ የተነሱና ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ በዚያች አገር በኩል ያቋረጡ መንገደኞች ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ ማድረግ ጀምራለች።

ዩናይትድ ኪንግደም ኬንያን ጨምሮ ከ30 በላይ ከሆኑ አገራት የሚነሱ ወይም ላለፉት 10 ቀናት የተጓዘ ወይም በአገራቱ በትራንዚት ያለፉ ዓለም አቀፍ መንገደኞች ወደ ግዛቷ እንዲገቡ አትፈቅድም።

ይህ ዕገዳ የብሪታኒያና የአየርላንድ ፓስፓርት ያላቸውን እንዲሁም የዩናይትድ ኪንግደም የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸውን መንገደኞች አይመለከትም ተብሏል።

ነገር ግን ተጓዦቹ ወደ አገር ሲገቡ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ፍቃድ በሰጣቸው ለለይቶ ማቆያነት በተዘጋጁ ሆቴሎች ውስጥ ለ10 ቀናት የመቆየት ግዴታ ይኖርባቸዋል። ክፍያውንም ቀድመው ይፈፅማሉ።