ጎርፍና መሬት መንሸራተት በኢንዶኔዢያና ምሥራቅ ቲሞር ከመቶ በላይ ሰዎች ሞቱ

በከባድ ጎርፍ የተመታችው የምሥራቅ ቲሞር ዋና ከተማ ዲሊ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ,

በከባድ ጎርፍ የተመታችው የምሥራቅ ቲሞር ዋና ከተማ ዲሊ

በኢንዶኔዢያና ምሥራቅ ቲሞር እሁድ ዕለት በደረሰ የጉርፍ መጥለቅለቅና የመሬት መንሸራተት አደጋ ቢያንስ 101 ሰዎች እንደሞቱ ተሰማ።

በደቡብ ምሥራቅ እስያ የጣለው ከባድ ዝናብ ግድቦች ከልክ በላይ ሞልተው እንዲፈሱና በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች በጉርፍ እንዲዋጡ ምክንያት ሆኗል።

በከባድ ዝናብና በጎርፍ የተመታው አካባቢ ከምሥራቃዊ ኢንዶኔዥያ ፍሎሬስ ደሴት እስከ ምሥራቅ ቲሞር ያለውን አካባቢን ያካልላል።

በአደጋው ኢንዶኔዢያ ውስጥ ብቻ 80 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ያሉበትን ማወቅ እንዳለተቻለ ተነግሯል። የአገሪቱ ባለሥልጣናት የአደጋው ሰለባዎች ቁጥር ከዚህ ሊልቅ እንደሚችል ገልፀዋል።

የኢንዶኔዢያ የአደጋ መከላከል መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ራዲቲያ ጃቲ "ጭቃና አስቸጋሪው የአየር ሁኔታ እንዲሁም የተከማቸ ቆሻሻ የፍለጋውንና የንፍስ አድን ሥራውን ፈታኝ አድርጎታል" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የምሥራቅ ፍሎሬስ አደጋ መከላከል ኤጀንሲ ባልደረባ የሆኑት አልፎንስ ሃዳ ቤታን ደግሞ "ብዙ ሰዎች ፍርስራሾች ውስጥ ተቀብረው ሊሆን እንደሚችል እንጠረጥራለን። የት እንዳሉ የማይታወቁ ሰዎች በቁጥር ምን ያህል እንደሆነ አይታወቅም" ብለዋል።

"በአደጋው የተፈናቀሉ ሰዎች ተበታትነዋል። በእያንዳንዱ ንዑስ አውራጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከአደጋው የሸሹ ሰዎች አሉ። በቤታቸው ውስጥ ደግሞ መድኃኒትና ምግብ የሚፈልጉም ይገኛሉ" ሲሉም ጨምረዋል።

በሌላ በኩል በምሥራቅ ቲሞር ወይም ቲሞር ሌሴ ታብላ በምትታወቅ ከፊል ደሴታማ አገር በአደጋው ቢያንስ 21 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱን የመንግሥት ባለስልጣናትን ጠቅሰው የዜና ወኪሎች ዘግበዋል።

የአደጋው ሰለባ ከሆኑት መካከል የአገሪቱ መዲና የሆነችው የዲሊ ነዋሪዎች እንደሚያመዝኑ ይታመናል።

የኢንዶኔዢያው ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊዶዶ የተሰማችውን ሐዘን ገልፀው ዜጉች በከባድ የአየር ሁኔታ ወቅት ከመንግሥት ባለስልጣናት የሚተላለፉ ምክሮችን እንዲተገብሩ አሳስበዋል።

"የአደጋ መከላከል ሥራው ውጤታማ እንዲሆንና በፍጥነት እንዲከወን ትዕዛዝ አስተላልፌያለሁ። ለአብነት ለጤና አገልግሎት፣ ለሎጀስቲክስ አቅርቦትና ለተፈናቀሉ ሰዎች መሰረታዊ ፍላጉት አቅርቦት እንዲሁም የመሰረተ ልማት መልሶ ግንባታ የተመለከቱት ይጠቀሳሉ" ብለዋል።

በዝናባማ ወቅቶች በኢንዶኔዢያ ጉርፍና የመሬት መንሸራተት እንግዳ የሆነ ክስተት አይደለም።

በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ ሱመዳንግ በተባለ ከተማ የጎርፍ መጥለቅለቅ ባስከተለው አደጋ 40 ሰዎች ሞተዋል።

መስከረም ላይ ደግሞ ቦርኒዮ በተባለ አካባቢ ቦታ መሬት ተንሸራቶ 11 ሰዎች ሞተዋል። ከዚህ ክስተት ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ደግሞ ሱሎዌሲ በተባለ ስፍራ በርካቶች በተመሳሳይ አደጋ ሞተው ነበር።

የአገሪቱ የአደጋ መከላከል አጀንሲ እንዳስቀመጠው ግምት ግማሹ የአገሪቱ ሕዝብ ወይም 125 ሚሊዮን ሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ስጋት ባለበት ስፍራ ላይ ይኖራል።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ,

ኢንዶኔዢያ ውስጥ ጎርፉ ያስከተለው ጉዳት