ፈረንሳዊው ቢሊየነር በፓሪስ ተደብድበው ተዘረፉ

ፈረንሳዊው ቢሊየነር በርናንድ ታፒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፈረንሳዩ ቢሊየነር በርናንድ ታፒ በፓሪስ ኩምላቪል መኖርያ ቤታቸው ውስጥ ሳሉ ነው ዘራፊዎች ገብተው የደበደቧቸው፡፡ ባለቤታቸውም ክፉኛ ተጎድተዋል፡፡

ቢሊየነሩ በርናንድ ታፒ የዝነኛው የአዲዳስ የስፖርት ትጥቅ አምራች የቀድሞ ባለቤት ናቸው፡፡

የቢሊየነሩን ቤት የደፈሩት ዘራፊዎች ቁጥርና ማንነት እስከአሁን አልታወቀም፡፡

ዘራፊዎቹ ቢሊየነሩን በርናንድ ታፒ እና ባለቤታቸው ሌሊት ላይ ከእንቅልፋቸው ቀስቅሰው በኤሌክትሪክ ገመድ ካሰሯቸው በኋላ ነበር ጠቀም ያለ ገንዘብ ለመዝረፍ የሞከሩት፡፡

ሆኖም በቢሊየነሩ ቤት እምብዛምም የፈለጉትን አላገኙም፡፡

የታፒንና ባለቤታቸውን የወርቅ ጌጣጌጦች ግን ሰብስበው ወስደዋል፡፡

የ78 ዓመቱ በርናንድ ታፒ በፈረንሳይ አወዛጋቢ ባለሀብትና ፖለቲከኛ ናቸው፡፡

ሽቅርቅርና ሁሌም የሚዲያ መነጋገርያ መሆን የሚወዱት ታፒ ከዚህ ቀደም ሚኒስትር ነበሩ፡፡

በተለይ ዝነኛውን የአዲዳስ ኩባንያን ከመሸጣቸው ጋር ተያይዞ ስማቸው በሙስና ተደጋግሞ ይነሳል፡፡

የ70 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ባለቤታቸው ወ/ሮ ዶሚኒክ እና ቢሊየነሩ በርናንድ ታፒ ሌሊት 6 ሰዓት ተኩል ግድም በተኙበት ነው ቢያንስ ከ4 በላይ የሆኑ ዘራፊዎች የቤታቸውን አጥርና የጥበቃ ሰንሰለቱን አልፈው በመግባት በቁጥጥር ያዋሏቸው፡፡

ይህ የሆነው ደግሞ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ሌሊት ነው፡፡

ዘራፊዎቹ ቢሊየነሩን በርናንድን ጸጉራቸውን ይዘው መሬት ለመሬት እየጎተቱ ከወሰዷቸው በኋላ ውድ ጌጣጌጦችንና የሚያስቀምጡበትን ቦታ እንዲጠቁሟቸው ሞክረዋል፡፡

ሆኖም ቤት ያስቀመጡት እዚህ ግባ የሚባል ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣ ንብረት ባለመኖሩ ዘራፊዎቹ ከፍተኛ ብስጭት ውስጥ እንደከተታቸው ተነግሯል፡፡ በዚህ ብስጭትም ቢሊየነሩን በዱላ ነርተዋቸዋል፡፡

በዚህ መሀል የ70 ዓመት ባለቤታቸው ወ/ሮ ዶሞኒክ ዘራፊዎቹን አምልጠው ለጎረቤት ቤታቸው እየተዘረፈ መሆኑን በማሳወቃቸው ፖሊስ ደርሶ አድኗቸዋል፡፡

ባለቤታቸው በዘራፊዎቹ ክፉኛ በመደብደባቸው አሁን ሆስፒታል ነው የሚገኙት፡፡

ሌቦቹ እስከ አሁን ወሰዱ የተባለው 2 ውድ ሮሌክስ የእጅ ሰዓቶችን፣ የጆሮ ጌጦችን፣ የእጅ አምባሮችን እና ቀለበቶችን ብቻ ነው፡፡

በርናንድ ታፒ ማን ነበሩ?

ቢሊየነሩ በርናንድ ታፒ ከ1992 እስከ 93 የፈረንሳይ የከተማ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ነበሩ፡፡

የታዋቂው የስፖርት ቁሳቁስ አምራች አዲዳስ ከፍተኛ የአክስዮን ባለቤት ነበሩ፡፡

በኋላ ደግሞ የዝነኛው የኦሎምፒክ ዴ ማርሴይ የእግር ኳስ ቡድን ባለቤት ሆነዋል፡፡

ላ ፕሮቬንሴና ሌሎች በርካታ ሚዲያዎችንን በባለቤትነት አስተዳድረዋል፡፡

እሳቸውም ቢሆን በመተወን፣ በመዝፈን እና የራዲዮና የቴሌቪዥን ትዕይነት በማሰናዳት ዝነኛ ነበሩ፡፡

በ1990ዎቹ ኩባንያቸው ኪሳራ በማወጁ ከሒሳብ ማጭበርበር፣ ከግብር ስወራና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተከሰው 5 ወራት እስር አሳልፈዋል፡፡

በርናንድ ላለፉት 20 ዓመታት በፍርድ ቤት ከአዲዳስ ኩባንያ ሽያጭ ጋር በተያያዘ እየተካሰሱ ይገኛሉ፡፡ ኩባንያውን በወቅቱ የሸጡት በግማሽ ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡