ኤልጂ በኪሳራ ምክንያት ከስማርት ስልክ ምርት መውጣቱን አስታወቀ

ኤልጂ ስማርት ስልክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኤልጂ ኤሌክትሮኒክስ ሰኞ ዕለት ኪሳራ እያስከተለበት ያለውን የስማርት ስልክ ንግዱን እንደሚዘጋ አስታወቀ።

የደቡብ ኮሪያው ግዙፍ የኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያ በታኅሣሥ ወር ላለፉት ስድስት ዓመታት የ4.5 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ያስከተለበትን ዘርፍ በተመለከተ የተለያዩ አማራጮችን ሲፈልግ እንደነበር አስታውቆ ነበር።

ኤልጂ እኤአ በ2013 ሦስተኛው ትልቁ ስማርት ስልክ አምራች የነበረ ሲሆን፣ በተለያዩ አቅጣጫዎች ምስል ማንሳት የሚችሉ ካሜራዎችን ጨምሮ በርካታ ፈጠራዎችን ለዓለም አበርክቷል።

ነገር ግን የኩባንያው አለቆች የተንቀሳቃሽ ስልክ ገበያ "እጅጉን ውድድር የበዛበት" መሆኑን ገልፀዋል።

ሳምሰንግ እና አፕል ሁለቱ ግዙፍ የስማርት ስልክ አምራቾች ሲሆኑ ኤልጂ ደግሞ በሃርድዌር እና ሶፍትዌሮቹ የተነሳ በርካታ ተግዳሮቶች ገጥመውት ነበር።

ኤልጂ ከኪሳራ ጋር እየታጋለ ባለበት ወቅት የተወሰነውን የንግዱን ክፍል ለመሸጥ የሞከረ ቢሆንም አልተሳካለትም።

በሰሜን አሜሪካ አሁንም ስሙ በሦስተኛ ደረጃ የሚነሳ ዝነኛ ብራንድ ቢሆንም ፊቱን ወደሌላ አዙሯል።

ኤልጂ ስልኮች በደቡብ ኮርያ አሁንም ሰፊ ተጠቃሚዎች አሏቸው።

ኩባንያው በመግለጫው "ኤልጂ ውድድር ከበዛበት የተንቀሳቃሽ ስልክ ገበያ ለመውጣት ያሳለፈው ስትራቴጂካዊ ውሳኔ ኩባንያው ሃብቱን በሌሎች ሊያድጉ በሚችሉ ዘርፎች ላይ. . . እንዲያተኩር ያደርገዋል" ብሏል።

ኤልጂ ባለፈው ዓመት 28 ሚሊዮን ስልኮችን ለገበያ ያቀረበ ሲሆን ተፎካካሪው ሳምሰንግ ግን 256 ሚሊዮን ስልኮችን ለሽያጭ ማቅረቡን ካውንተርፖይንት የተሰኘ ድርጅት የሰራው ጥናት ያሳያል።

ኤልጂ ከተሰማራባቸው አምስት ዘርፎች መካከል ስማርት ስልኮች አነስተኛ ድርሻ ሲኖራቸው፣ የኩባንያውንም 7.4 በመቶ ገቢን ይሸፍናሉ።

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የተንቀሳቃሽ ስልክ ገበያ ድርሻው 2 በመቶ ብቻ ነው።

ኤልጂ የግዙፎቹን ተቀናቃኞቹን ገበያ ለመሻማት የተለያዩ ፈጠራዎችን እየሞከረ የነበረ ሲሆን ባለፈው ዓመት ቲ ቅርጽ ያለው፣ በአንድ ጊዜ ሁለት ነገርን መስራት የሚያስችል ሰፊ ስክሪን ያለው ስማርት ስልክ አስተዋውቆ ነበር።

ኤልጂ አሁንም በኤክትሮኒክስ ንግድ ዘርፍ ጠንካራ ተፎካካሪ ሲሆን የሚያመርተው ቴሌቪዥን በሽያጭ ከሳምሰንግ በመቀጠል ሁለተኛ ነው።

በኅዳር ወር ከአውቶሞቲቭ አቅራቢው ማግና ኢንተርናሽናል ጋር የኤሌትሪክ መኪኖች መለዋወጫዎችን ለማቅረብ ስምምነት ፈርሟል።

ኤልጂ የስማርት ስልክ ንግዱን ቢዘጋም ለደንበኞቹ አስፈላጊውን አገልግሎት ማቅረቡን እንደሚቀጥል ተናግሯል።