ኡበር ታክሲን የከሰሰችው ዓይነስውር ሴት 1 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ተፈረደላት

ኡበር በበኩሉ ሾፌሮቼ ተቀጣሪ ሰራተኞቼ ሳይሆኑ ኮንትራት የወሰዱ ግለሰቦች ናቸው፤ ለጥፋቱ እኔ ሳልሆን ሾፌሮቹ ናቸው መጠየቅ ያለባቸው ሲል ተከራክሯል፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፍርድ ቤት ኡበር ኩባንያ ለአንዲት ዓይነስውር 1 ሚሊዮን 1 መቶ ሺህ ዶላር እንዲከፍል ፈረደበት፡፡

ኡበር ይህን ያህል መጠን ያለው ካሳ እንዲከፍል የተፈረደበት 14 ጊዜ ያህል ታክሲ ፈልጋ ገሸሽ በመደረጓ ነው፡፡

ከሳሽ ሊዛ አርቪንግ እንዳለችው አንዳንድ የኡበር ሾፌሮች ክብሯን ዝቅ አድርገው አዋርደዋታል፡፡ ይህም የሆነው ዓይነስውር በመሆኗ መንገድ የምትመራትን ውሻ ላለማሳፈር ብለው ነው፡፡

አንድ የኡበር ሾፌር ደግሞ በሐሰት መወረጃሽ ደርሷል ብሎ ግማሽ መንገድ ላይ ከታክሲው አስወርዶኛል ብላለች፡፡

ገለልተኛ የገላጋይ ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን ዓይነ ስውሯ የኡበር ደንበኛ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ መገለል ደርሶባታል በሚል ፍርድ ሰጥቷል፡፡

ኡበር በበኩሉ ሾፌሮቼ ተቀጣሪ ሰራተኞቼ ሳይሆኑ ኮንትራት የወሰዱ ግለሰቦች ናቸው፤ ለጥፋቱ እኔ ሳልሆን ሾፌሮቹ ናቸው መጠየቅ ያለባቸው ሲል ተከራክሯል፡፡

የሳንፍራሲስኮ ነዋሪዋ ሊዛ አርቪንግ ኡበር ታክሲ በምትጠራበት ጊዜ ብዙዎቹ እሷን ለማሳፈር ፍቃደኞች ስላልሆኑ በተለይ በምሽት ሕይወቷን አደጋ ላይ ጥለውት ያውቃሉ፡፡

ብዙውን ጊዜ ኡበር ስትጠራ ውድቅ ስለሚደረግባትም ለበርካታ ቀጠሮዎች መዘግየትና ለሥራ አርፍዶ መግባት ዳርጓታል፡፡

ይህ እንግልት እየደረሰባትም ለኡበር ጉዳዩን በተደጋጋሚ አመልክታ ቸል መባሏ ወደ ክስ እንድትሄድ እንዳስገደዳት ተናግራለች፡፡

የሊዛ አርቪንግ ቃለ አቀባይ እንዳሉት በአሜሪካ የአካል ጉዳተኞች ደንብ ላይ ዓይነስውራንን የሚመሩ ዉሾች ባለቤቶቹ የሚሄዱበት ቦታ ሁሉ የመግባት መብት አላቸው፡፡

ኡበር ግን ይህን እያከበረ አይደለም ሲሉ ከሰዋል፡፡

የካሳውን ውሳኔ ተከትሎ የኡበር ኩባንያ ለዓይነስውራን በሚሰጠው አገልግሎቱ ኩራት እንደሚሰማው ጽፏል፡፡

የኡበር ሾፌሮችንም ከአካል ጉዳተኛ ደንበኞች ጋር በተያያዘ ስልጠና መስጠታችንን እንቀጥላለን ብሏል ኡበር፡፡

ሊዛ ለሳንፍራንሲስኮ ክሮኒክል ጋዜጣ ፍርዱን በተመለከተ በሰጠችው አስተያየት እኔ ከገንዘቡ ይልቅ መብቴ ቢከበርልኝ ነው የምመርጠው ሆኖም ቅጣቱ ጥሩ መልእከት ያስተላልፋል ብላለች፡፡