ኮሮናቫይረስ፡ ለኮቪድ-19 እጅ አልሰጥ ያለችው ጉሊት ቸርቻሪ

ጆሴፊንና ልጆቿ

የፎቶው ባለመብት, JOSEPHINE MUCHILWA

ጆሰፊን ትባላለች። ኮሮና ወረርሽኝ ሲቀሰቀስ ሰው ቤት በሠራተኝነት ትሠራ ነበር።

ከዚያ ሃብታሞች እንሞታለን ብለው ፈሩ። ድሆች ቫይረሱን ተሸክመው ቤታችን ይመጡብናል ብለው ሰጉ። ሠራተኞቻቸውን አባረሩ።

ጆሰፊንም ተባረረች። ሥራ ፈታች።

ምን ትብላ? የሚላስ የሚቀመስ ጠፋ። የእርሷ ብዙ አያሳስብም። ለምግብ ያላነሱ፣ ለሥራ ያልደረሱ አራት ልጆች አሏት። ተራቡ።

"ወደ ሰማይ አንጋጠጥኩ አምላኬ ሆይ! ስለምን ተውከኝ! ስል ተጣራሁ" ትላለች የ31 ዓመቷ ጆሰፊን።

ይህን ፍዳዋን በራዲዮ ቢዝነስ ዴይሊ ተናገረች።

ብዙ አድማጭ እና መራብ ብርቅ ነው እንዴ ያለ መሰለ። አንድ ሁለት አድማጮች ግን ልባቸው ተነካ። ገንዘብ አዋጡ። ብዙ አይደለም። 150 ዶላር። ለሷ ግን ብዙ ነበር።

ጉሊት ከፈተች። ጎመን፣ ቲማቲምና ሽንኩርት መሸጥ ጀመረች።

በአውቶቡስ ከናይሮቢ ወጣ ብሎ ወደሚገኝ የከተማ-ገጠር ትሄድና አትክልትና ፍራፍሬ በጅምላ በጆንያ ገዝታ ተሸክማ ትመጣለች። ኪቢራ ሰፈር ስትደርስ ታራግፈዋለች።

ኪቢራ ሙልጭ ያሉ ድሆች መኖርያ ነው።

ያመጣችውን ዘርግታ ትቸረችራለች። አለበለዚያ እሷም አራቱ ልጆቿም በረሀብ ማለቃቸው ነው።

ጆሴፊን ጉሊቷ ቁጭ ብላ አንድ አምስት ደንበኛ አስተናግዳ ገበያው ጭር ሲል የድምጽ መልዕክት ታስተላልፋለች፣ ወደ ራዲዮ ጣቢያ። ልፋቷን፣ ድካሟን ተስፋዋን ለአድማጮች ታጋራለች። 150 ዶላር ለሰጧትም ላልሰጧትም።

ኪቢራ በኬንያ ትልቁ የድሆች መንደር ነው፡፡ ብዙዎቹ የኪቢራ ነዋሪዎች የቤት ሠራተኛ፣ የቆሻሻ ጠራጊ እና በለስ የቀናቸው ደግሞ ሾፌር ሆነው ነው የሚቀጠሩት።

ወረርሽኙ ሁሉንም አሽመድምዷል። ኪቢራዎችን ግን ክፉኛ ደቁሷቸዋል።

ጆሴፊን ልጆቿን በረሀብ ከመሞት ታደገቻቸው። ዕድሜ ለራዲዮ አድማጮች። 150 ዶላር ባይሰጧት ይህን ጊዜ ምን ይውጣት ነበር?

አሁን በቀን ቢያንስ 10 የሚሆኑ ደንበኞች መጥተው ይገዟታል።

የፎቶው ባለመብት, JOSEPHINE MUCHILWA

"ዛሬ ለምሳሌ 170 ሽሊንግ (1 ዶላር ከ50 ሳንቲም አካባቢ) አትርፊያለሁ። አሁን ልጆቼም ቀማምሰው ይተኛሉ፤ ክብሩ ይስፋ" ብላ ነበር ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር አካባቢ።

ኪቢራ የድሆችን መንደር ብቻ ሳይሆን የወንጀሉም ብዛት የትየለሌ ነው። ሴቶች ቀን በቀን ይደፈራሉ። ቀማኞች በጭርንቁሱ ሰፈር ይደበቃሉ። ፖሊስ ሁልጊዜ አሰሳ ያደርጋል። በዚያ ላይ ሰዓት እላፊው አለ። በዚያ ላይ ጆሰፊን ከዚያ በፊት ቢዝነስ ሞክራ እንኳ አታውቅም።

"በኪቢራ ሴት ልጆችን መድፈር የዘውትር ተግባር ነው። ልጆቼን ቤት ትቻቸው ከወጣሁ አደጋ ይደርስባቸዋል" ትላለች ጆሰፊን። ስለዚህ ከጉሊቷ ጋር ልጆቿንም ትጎልታቸዋለች።

ሌላው ችግር ኪቢራ ውስጥ ብዙ ሰው ሽንኩርትና ቲማቲም ለመግዛት ገንዘብ የለውም። ስለዚህ ብዙ ደንበኛ ማፍራት አልቻለችም።

ጆሰፊን የሞት ሽረት ትግል እያደረገች ሳለ ኮቪድ-19ን ታግላ ልትጥለው ስትል ክፉ እጣ ገጠማት። ወባ ታመመች። መታከምያ አልነበራትም።

ወባ መድኃኒት ይፈልጋል። ምግብ ይፈልጋል። እሷ ቤሳ ቤስቲን የላትም። ከኪቢራ የሰፈር አራጣ አበዳሪዎች ለሕክምና ገንዘብ ተበደረች።

የሰፈሩ አራጣ አበዳሪዎች ተማርረዋል። ሰዎች ገንዘብ ተበድረው አይመልሱም። ስለዚህ ቤት ውስጥ ያላቸውን ጥሪት መያዣ ካላመጡ ማበደር ትተዋል። ጆሰፊን ደግሞ ጥሪት የሚባል አልነበራትም። ብድሩን ግን ከዚያም ከዚህ ብላ አሳካች።

በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ሳለች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ጉሊቱ ፈረሰባት። መንግሥት የባቡር ማስፋፊያ ብሎ ቦታዋ ለልማት እፈልገዋለሁ አለ። በአንድ ቀን አባረራት። ትንሽዋ ጉሊት ፈረሰች።

አሁን የተበደረችው 30 ዶላር አልመለሰችም። አበዳሪዎቿ ሊገድሏት ይችላሉ። በኪቢራ ቀልድ የለም። ገንዘብ ሁሉ ነገር ነው። ሕይወትም ነው፤ ሞትም ነው።

ጆሴፊን ጉሊቷ ውስጥ አንዳንድ ነገሮችን አከማችታ ነበር። ሱቋ ትፈርሳለች ብላም አላሰበችም።

ሱቋ ውስጥ ከነበረው ሽንኩርትና ቲማቲም ጭምር ነው መጥተው ያረሱት። መንግሥት በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሰጥቻለሁ ቢልም ጆሰፊን ግን በጭራሽ ትላለች።

"ያን ቀን ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ። ሦስት ቀን ሙሉ አለቀስኩ። ልጆቼ በድጋሚ ተራቡብኝ።"

በኬንያ በይፋ የተነገረው 2 ሺህ ሰዎች በኮቪድ መሞታቸው ታውቋል። ነገር ግን ቁጥሩ ከዚህ የትና የት እንደሚጨምር ይታመናል።

የኪቢራ የድሆች ሰፈር ነዋሪዎች በኮቪድ ክፉኛ ነው የተጎዱት። ወረርሽኙ ማጅራታቸውን ነው የመታቸው። ሆኖም እጅ አልሰጡም።

"እነዚህ ብዙዎቹ በቀን ከ2 ዶላር በታች የሚያገኙ ነዋሪዎች ናቸው። ከታመሙ እንደሚሞቱ ያውቃሉ። ረሀብም እንደሚገድላቸው ያውቃሉ" ይላል የኪቢራ ተወላጅና የሻይኒንግ ሆፕ በጎ አድራጎት ድርጅት ባልደረባ ኬኔዲ ኦደዲ።

አሁን ወረርሽኙ ዓመት አልፎታል። ጆሰፊን አሁንም ትግል ላይ ናት። ላለመሞት። ምንም ዓይነት ቋሚ ገቢ የላትም። ልጆቿ ከዚያም ከዚህ ብለው ልቅምቃሚ በልተው ያድራሉ።

"ወደፊት ዶክተር እሆናለሁ፣ አሁን ግን የሚበላ ነገር ነው የምፈልገው" ትላለች የ11 ዓመት የጆሰፊን የበኩር ልጅ፣ ሻሚም።

ጆሰፊን አራቱንም ልጆቿን ይዛ እየታገለች ነው። ላለመሞት-በኮቪድም በረሀብም።