ኮሮናቫይረስ፡ በሩዋንዳ የኮቪድ-19 መመሪያን የጣሱ ሙሽሮች ውጭ እንዲያድሩ ተደረጉ

ውጭ ያደሩት ሙሽሮች

የፎቶው ባለመብት, RwandaTelevision

በሩዋንዳ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት የወጡ መመሪያዎችን ጥሰዋል የተባሉ ሙሽሮችና ቤተሰቦቻቸው ውጭ እንዲያድሩ መገደዳቸው ተገልጿል።

መመሪያውን ጥሰው ሰርግ አድርገዋል የተባሉ ሙሽሮች በሰርጋቸው ምሽት ውጭ እንዲያድሩ መደረጉ ከፍተኛ ትችትን አስነስቷል፤ በርካታ ሩዋንዳውያንን አስቆጥቷል።

ይህንንም የሚያሳየው ቪዲዮ በርካቶች ተጋርተውታል።

ስሜ አይገለፅ ያለችው ሙሽሪት ለቢቢሲ እንደተናገረችው ምሽቱን በስታዲየም ማሳለፏን በተመለከተ "የሰርጌን ምሽት በእንደዚህ ሁኔታ ውጭ ማሳለፌ መቼም ቢሆን በህይወቴ የማልረሳው መጥፎ ትዝታ ነው" ብላለች።

አክላም "በዚህ መንገድ ሰዎችን ማዋረድና ማሳፈር ኮሮናቫይረስን እንድንፈራ ወይም መመሪያዎቹን እንድናከብር አያደርገንም" በማለት አስረድታለች።

በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ የፈረንጆቹን የትንሳኤ ክብረ በዓል አስመልክቶ ሊደረጉ የነበሩ ሶስት ሰርጎችን ፖሊስ አስቁሜያለሁ ብሏል። ለዚህም መመሪያው ከሚያዘው 20 ታዳሚዎች በላይ መሆኑ ጋር ተያይዞ ነው ተብሏል።

የፖሊስ ቃለ አቀባይ ለሩዋንዳ ሚዲያ እንደተናገሩት "በርካቶች መመሪያዎችን በመጣስ ዝግጅቶችን እያደረጉ ነው" ፖሊስም እንዲህ አይነት ጥሰቶችን በዝምታ አይመለከትም ብለዋል።

ሙሽሮቹ የሰርጋቸውን ምሽት በስታዲየም ማሳለፋቸውን በርካቶች በበይነ መረብ ያወገዙት ሲሆን ህግ አስከባሪዎች ያልተገባ ስራ ሰርተዋል ብለዋል።

ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ሰዎችን ይዘው ምሽቱን በስታዲየም እንዲያሳልፉ አድርገዋል በማለት የተቹ እንዳሉ ሁሉ ለህዝቡ ደህንነት ነው በማለት ያሞካሹት አልታጡም።

ክላሪስ ካራሲራ የተባለች የሩዋንዳ ሙዚቀኛ በበኩሏ "ሰብዓዊነትን ያጣ እንዲሁም ለተጣማሪዎቹም ሆነ ለወደፊት ልጆቻቸው ከፍተኛ ህመምን" የሚፈጥር ነው በማለት በትዊተር ገጿ አስፍራለች።

ሩዋንዳ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት ያወጣቻቸው መመሪያዎች በአለም አቀፍ ደረጃ የተወደሰ ቢሆንም ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ተቃዋሚዎች በበኩላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው በማለት ይከራከራሉ።

አገሪቷ ወረርሽኙ ከተከሰተባት ዕለት ጀምሮ 22 ሺህ የኮሮናቫይረስ ህመምተኞችን የመዘገበች ሲሆን እስካሁንም 311 ዜጎቿን አጥታለች።