ሱዳን የኢትዮጵያ ጦር ከአብዬ ግዛት እንዲወጣ የተባበሩት መንግሥታትን ጠየቀች

አንድ ሠላም አስከባሪ

የፎቶው ባለመብት, United Nations Peacekeeping/FB

በአወዛጋቢው የአብዬ ግዛት ውስጥ በሠላም አስከባሪነት የተሰማራው የኢትዮጵያ ሠራዊት በሌላ አገር ጦር እንዲተካ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታትን መጠየቋ ተነገረ።

የሱዳን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት "የኢትዮጵያ ሠራዊት በምሥራቃዊ የሱዳን ድንበር አካባቢ እየተጠናከረ ባለበት ጊዜ ስትራተጂክ በሆነው የሱዳን ማዕከላዊ ስፍራ ላይ የኢትዮጵያ ኃይሎች እንዲኖሩ መፍቀድ ምክንያታዊ አይሆንም" ማለቱን ዜና ወኪሉ ዘግቧል።

የሱዳን ዜና ወኪል የአገሪቱን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም አል ሳዲቅ አል መሐዲ ይህንን ተናግረውታል ያለው በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲደረግ የነበረው ድርድር ውጤት ሳያመጣ ከተጠናቀቀ በኋላ ከአንድ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።

ሱዳንና ኢትዮጵያን ለዓመታት በይገባኛል ጥያቄ ሲያወዛግብ የነበረውን የድንበር አካባቢ ከአምስት ወራት በፊት ሰራዊቷን አሰማርታ በቁጥጥሯ ስር ማስገባቷን የገለጸች ሲሆን፤ ኢትዮጵያም እርምጃውን አውግዛ ችግሩ በውይይት እንዲፈታ በተደጋጋሚ ስትጠይቅ ቆይታለች።

ኢትዮጵያና ሱዳን ከድንበር ውዝግቡ በተጨማሪ ግንባታው ወደ መጠናቀቁ በተቃረበው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያም ያላቸውን አለመግባባት ለመፍታት በተደጋጋሚ ሲያደርጉት የቆየው ድርድር ምንም ውጤት ሳያስገኝ ቆይቷል።

ሱዳን ከግብጽ ጋር በመቆም ሁለቱ አገራት በግድቡ የውሃ አሞላልና ቀጣይ ሥራ ዙሪያ በሚደረገው ድርድር ላይ ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር ጥረት እያደረጉ ሲሆን፤ 85 በመቶ የወንዙን ውሃ የምታመነጨው ኢትዮጵያም ጠንካራ አቋም በመያዝ "ብሔራዊ ጥቅሟን የሚጎዳ ስምምነት ውስጥ እንደማትገባ" አሳውቃለች።

በዚህም የሱዳኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪንሻሳ ላይ በተካሄደው ውይይት ወቅት ኢትዮጵያ "ተቀባይነት የሌለው ግትርነትን" በማሳየት "ከዓለም አቀፍ ሕግ በተጻረረ ሁኔታ" የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወን ወስናለች ሲሉ ወቀሳ ሰንዝረዋል።

በግድቡ ድርድር ስምምነት ባለመደረሱና ከሱዳን ጋር ባለው የድንበር ጥያቄ ምክንያት "የተባበሩት መንግሥታት አብዬ ውስጥ ያሰማራውን የኢትዮጵያን ጦር በሌላ እንዲተካ ሱዳን ጥያቄ አቅርባለች" ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ ጨምረውም ሱዳን ጨምረውም አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የግንኙነትና የትብብር ስምምነቶችን መለስ ብላ እየመረመረች መሆኑን ገልጸው፤ ነገር ግን ይህ ስደተኞችን ጨምሮ በአገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚመለከት አይደለም ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያመለክተው ከ3300 በላይ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት በድርጅቱ ዕዝ ስር በአብዬ ግዛት ውስጥ ተሰማርተው የሠላም ማስከበር ተግባር እያከናወኑ ይገኛሉ።

በግዛቲቱ የመቆያ ጊዜው ባለፈው ኅዳር ወር የተጠናቀቀው የሠላም አስከባሪው ሠራዊት አሁን ያለው በተራዘመለት የስድስት ወር ጊዜ ሲሆን ይህም በመጪው ግንቦት ወር የሚያበቃ ይሆናል።