ኪም ካርዳሺያን የናጠጡ ቢሊየነሮች ክበብን ተቀላቀለች

ኪም ካርዳሺያን ዌስት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ኪም ካርዳሺያን ዌስት

የአሜሪካ የቴሌቪዥን ትዕይንት ኮከብ ኪም ካርዳሺያን ዌስት የናጠጡ ሀብታሞች ተርታ መግባቷን ፎርብስ መጽሔት አወጀላት።

የኪም ካርዳሺያን የተጣራ ሀብቷ 1 ቢሊዮን ዶላር ደርሶላታል። በዋናነት የመዋቢያ እቃዎች ምርትና የማስታወቂያ ጉርሻ ለገቢዋ እዚህ መድረስ ሁነኛ ቦታ አላቸው።

አሁን ኪም ካርዳሺያን ዌስት ከዓለም ቢሊየነሮች ተርታ የባለጸጎች መዝገብ ላይ 2 ሺህ 755ኛ ሆና ተቀምጣለች።

በዚህ ዓመት ቢሊየነሮች ክበብን ከተቀላቀሉት መሀል የ'በብል' የፍቅር ጓደኛ አጣማሪ መተግበሪያ ፈጣሪ ዊትኒ ዎለፍ ህርድ በ1.3 ቢሊዮን ዶላር፣ የፊልም ጥበበኛ ታይለር ፔሪ በአንድ ቢሊዮን ዶላር፣ የካሲኖ አቋማሪ ድርጅት ባለቤት የነበሩት የሼልደን አደልሰን ሚስት ሚሪየም አደልሰን በ38 ቢሊዮን ዶላር አዱኛ ዝርዝር ውስጥ ይገኙበታል።

ይህንን የናጠጡ ቢሊየነሮች ክበብን የአማዞኑ ጄፍ ቤዞስ በበላይነት በ177 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ገቢ ይመራዋል።

ከኪም ካርዳሺያን ጋር አብሮ መኖር ያቆመው አቀንቃኙ ካኒዬ ዌስት ከኪም ቀደም ብሎ በ1.8 ቢሊዮን ዶላር ይህን የቢሊየነሮች ክበብ ተቀላቅሏል።

ፎርብስ ዘንድሮ የኪምን ግማሽ እህት ኬሊ ጄነርን ከዚህ ክበብ ሰርዟታል። ምክንያቱ ደግሞ ገቢዋ ማሽቆልቆሉ ነው።

ፎርብስ 40 ዓመት የደፈነችውን ኪም ካርዳሺያንን ሀብት ከ780 ሚሊዮን ዶላር እንዴት ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር እንደደረሰ የገለጸ ሲሆን፤ ኬኬደብሊው የመዋቢያ እቃዎች ቢዝነሷና ስኪምስ የውስጥ ቅንጡ ልብስ ኩባንያዋ እንዲሁም ከማስታወቂያ ገቢ የተገኘ ረብጣ ዶላር ነው ምክንያቱ ብሏል።

ኪም ባለፈው ዓመት የኬኬደብሊው ኮስሞቲክን 20 ከመቶ ድርሻ 'ኮቲ' ለተሰኘው ስመ ጥር ኩባንያ በ200 ሚሊዮን ዶላር ሽጣው ነበር።

መዘነጫ የውስጥ ልብሶችንና ሸንቃጣ የሚያደርጉ አልባሳትን በመሸጥ የሚታወቀው ስኪምስ በዚህ ዓመት ስኬታማ ሆኖላታል።

ኪም የምርቶቹን ገበያ መቆጣጠር ያስቻላት ከ200 ሚሊዮን በላይ በኢኒስታግራም ተከታዮች ስላሏት ነው። በትዊተር ደግሞ 70 ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮችን አፍርታለች።

ኪም ባለፈው የካቲት ከሙዚቀኛው ካንዬ ዌስት ጋር ፍቺ መጠየቋ ተዘግቦ ነበር። ኪምና ካንዬ 7 ዓመታት በዘለቀ ጋብቻ 4 ልጆችን አፍርተዋል።