ሕዳሴ ግድብ፡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በኪንሻሳ ያደረጉት ውይይት ያለውጤት ተጠናቀቀ

የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ የመጠቀም ያላትን ተፈጥሯዊ መብትን የሚቃረን ማንኛውንም ስምምነት እንደማትፈርም አስታወቀች።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ያለውጤት ተጠናቋል።

ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ባወጣችው መግለጫ ነው "ብሔራዊ ጥቅሟን የሚጎዳ ስምምነት ውስጥ እንደማትገባ" በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂሚኒስቴር በኩል ይፋ ያደረገችው።

በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ "ፍትሃዊና ምክንያታዊ የሆነውን፣ የአሁንና የወደፊቱን የአባይን ውሃ የመጠቀም መብቷን የሚገድብ ማንኛውንም ስምምነት አትፈርምም" ሲል ሚኒስቴሩ የአገሪቱን አቋም ገልጿል።

ዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ በተካሄደው ደቡብ አፍሪካ፣ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት በታዛቢነት በተገኙበት በዚህ ድርድር ላይ የተለያዩ ጉዳዮች ተነስተው የሦስቱ አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በአፍሪካ ሕብረት አማካይነት ተወያይተዋል።

ከእነዚህም መካከል ኢትዮጵያ ድርድሩ ላይ ደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረትና አሜሪካ በታዛቢነት እንዲቀጥሉ የተስማማች ሲሆን ሱዳንና ግብጽ ግን ከአፍሪካ ሕብረት እኩል ሚና እንዲኖራቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም ተቀባይነት እንዳላገኘ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ይህንን ሃሳብ ውድቅ ያደረገቸው "የአፍሪካ ሕብረትን ሚና የሚያሳንስ ነው" በሚል እንደሆነ ሚኒስቴሩ ገልጾ፤ ነገር ግን ታዛቢዎቹ የድርድሩን ሂደት እንዲደግፉና ሦስቱም አገራት በጋራ ሲስማሙ ብቻ ሃሳብ እንዲያቀርቡ ተስማምታለች።

በውይይቱ ማብቂያ ላይ በዲሞክራቲክ ኮንጎና በአፍሪካ ሕብረት የቀረበውን ረቂቅ መግለጫ ኢትዮጵያ መቀበሏን ያመለከተው መግለጫው ግብጽና ሱዳን ግን ሳይቀበሉት ቀርተዋል በማለት "ሁለቱ አገራት ድርድሩ አውንታዊ ውጤት እንዳይኖረው እንቅፋት ሆነዋል" ሲል ወቅሷል።

ግብጽና ሱዳንም በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ጋር በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ሲያደርጉት የነበረው ውይይት ያለ ውጤት መጠናቀቁን በመግለጽ ኢትዮጵያን ተጠያቂ አድርገዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ሁለቱ አገራት ለድርድሩ የቀረበውን ሐሳብ ኢትዮጵያ ሳትቀበለው አንደቀረች መግለጻቸውን ዘግቧል።

"ይህ የኢትዮጵያ አቋም በቅን ልቦና ለመደራደር ፖለቲካዊ ፈቃደኝነቱ እንደሌላት በድጋሚ የሚያሳይ ነው" ሲል የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

የሱዳን መስኖና የውሃ ሀብት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ደግሞ "ይህ የኢትዮጵያ ግትር አቋም ሱዳን ሕዝቧንና ደኅንነቷን ለመጠበቅ ሌሎች አማራጮችን እንድትፈልግ ያደርጋታል" ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል።

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው እንደገና በተጀመረው በዚህ የሦስቱ አገራት ውይይት ላይ ከስምምነት ለመድረስ የሚያስችል እርምጃ ባለማሳየቱ ስኬታማ ሊሆን አልቻለም።

የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በድርድሩ ዙሪያ ማክሰኞ ማታ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው ግን ለድርድሩ ስኬታማ አለመሆን "ሱዳንና ግብጽ የያዙት ግትር አቋምን" እንደምክንያት አቅርቧል።

ሚኒስቴሩ በግድቡ አሞላል፣ ውሃ አያያዝ እንዲሁም አለቃቀቅን በተመለከተ ከስምምነት ለመድረስ ኢትዮጵያ ዝግጁ እንደሆነች ጠቅሶ፤ ነገር ግን "ሁለቱ አገራት ድርድሩ የኢትዮጵያን የውሃ ድርሻ የሚገድብና አለን የሚሉትን የውሃ ክፍፍል የሚያፀና አስገዳጅ ስምምነት ካልተደረሰ የሚል አቋም በመያዛቸው" ከውጤት አለመደረሱን ገልጿል።

ጨምሮም ግብጽና ሱዳን በተደጋጋሚ ሲሉት የነበረውን አስገዳጅ ስምምነት ሳይደረግ የግድቡ ሙሌት መከናወን የለበትም የሚለው ሃሳብ "የሕግ መሠረት የሌለውና ኢትዮጵያ የላትን የተፈጥሮ ሃብት የመጠቀም መብት የሚጋፋ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም" ሲል ውድቅ አድርጎታል።

በዚህም መሠረት የግድቡ ሁለተኛ ዓመት የውሃ ሙሌት ከዚህ በፊት በተደረሰው የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት በተያዘለት የጊዜ ሠሌዳ መሰረት ይካሄዳል ሲል የኢትዮጵያን አቋም በድጋሚ ይፋ ገልጿል።

በዲሞክራቲክ ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ የተካሄደው ድርድር ለሁለት ቀናት የታሰበ የነበረ ቢሆንም አገራቱ ከሚያስማማ ነጥብ ላይ መድረስ ስላልቻሉ ለሦስተኛ ቀን ማክሰኞ ዕለት ቀጥሎ ተካሂዶ እንደነበር ተነግሯል።

ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ተቋርጦ ቆይቶ አሁን የተካሄደው ድርድር ያለውጤት ቢጠናቀቅም በቀጣይ በሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ግንባታው ከተጀመረ አስረኛ ዓመቱን የያዘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና ቀጣይ የሥራ ሂደትን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል ለዓመታት ሲካሄድ የቆየው ድርድር ውጤት ሳያስገኝ እስከአሁን ዘልቋል።

አሁን የአፍሪካ ሕብረት በሚያሸማግለው ይህ ድርድር ቀደም ሲል በአዲስ አበባ፣ በካርቱም፣ በካይሮና በዋሽንግተን ላይ የሦስቱ አገራት ልዑካን ተገናኝተው ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ ከቆየ በኋላ በበይነ መረብ አማካይነት ቀጥሎ ነበር።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጭምር የተሳተፉበት የዋሽንግተኑ ድርድር ከስምምነት ለመድረስ ከጫፍ ደርሶ ነበር ተብሎ የተነገረለት ቢሆንም ኢትዮጵያ የቀረበው ሐሳብ ብሔራዊ ጥቅሜን የሚያስጠበቅ አይደለም ስትል ከፊርማው ራሷን አግልላለች።

ኢትዮጵያ አምስት ቢሊየን የሚጠጋ ዶላር አውጥታ እየገነባችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሊጠናቀቅ 20 በመቶ ያህል የቀረው ሲሆን፤ ግድቡ በአፍሪካ ካሉ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች በሙሉ ቀዳሚውነው ተብሏል።

ግድቡ ተጠናቅቆ ሙሉ ለሙሉ ሥራውን ሲጀምር ከ5ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም አለው።

ግድቡ ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ያደረገ ሲሆን ሁለተኛውን ዙር ደግሞ በመጪው ክረምት እንደሚከናወን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።

ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው የግድቡ የግንባታ ሥራ መከናወኑ የተነገረ ሲሆን በመጪው ዓመትም በተወሰነ ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል።

ግብጽና ሱዳን ግድቡ የውሃ አቅርቦታችንን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሰዋል በሚል ከግንባታው መጀመር አንስቶ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቢቆዩም፤ ከግማሽ በላይ ለሚሆነው ሕዝቧና እያደገ ላለው የኢንዱስትሪ ዘርፏ ኤሌክትሪክ ለማቅረብ ዋነኛ ግቧ አድርጋ የተሳችው ኢትዮጵያ በግንባታውና ቀጥላ ወደ ማጠናቀቁ ተቃርባለች።

የአባይ ወንዝን 85 በመቶ ውሃ የምታመነጨው ኢትዮጵያ፣ የግድቡን ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ከማከናወኗ በፊት አሳሪና ሕጋዊ ስምምነት እንድትፈርም እየወተወቱ ያሉት ሱዳንና ግብጽ ባቀረቡት ሐሳብ ላይ ሳትስማማ ቆይታለች።

የግብጽ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ ባለፈው ማክሰኞ፣ ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው ግድብ ሳቢያ አገራቸው በምታገኘው የውሃ መጠን ላይ ተጽእኖ የሚፈጠር ከሆነ 'የከፋ አካባቢያዊ ችግር' ይፈጠራል ሲሉ አስጠነቅቀው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ "ማንም ከግብጽ ውሃ ላይ አንዲት ጠብታ መውሰድ አይችልም፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሚታሰበው በላይ አደገኛ አለመረጋጋት በአካባቢው ይፈጠራል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን የምትጠቀመው ውሃውን በግዛቷ ውስጥ ለሚያስቀሩ ፕሮጀክቶች እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ብታስረዳም ሱዳን በተለይም ግብጽ የትኛውም አይነት በውሃው ላይ የሚከናወን ሥራ የእነሱን ይሁንታ ሳያገኝ መካሄድ እንደሌለበት ሲገልጹ ቆይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በአገሪቱ ምክር ቤት ላይ ባደረጉት ንግግር "ውሃ አሞላሉን በተመለከተ ተደራድረን ስናበቃ እንሙላ ካልን ክረምቱ ያልፍና በዓመት 1 ቢሊየን ዶላር እናጣለን" ሲሉ የውሃ ሙሌቱን ማዘግየት እንደማይቻል አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር የሆኑት ስለሺ በቀለ (ዶ/ር፣ ኢንጂ.) ኢትዮጵያ ወደ መጠናቀቁ የተቃረበውን የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በምንም ዓይነት መልኩ እንደማታራዝመውና ለዚህም የሚያበቃ አሰራርና ምክንያትም እንደሌለ ተናግረዋል።

ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በስልክ የተወያዩት የአሜሪካው ውጩ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን፣ አሜሪካ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ አለመግባበት በውይይትና ሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸው የሱዳን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

የህዳሴው ግድብ ውዘግብ በግብጽ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና እና በኢትዮጵያ ለሚኖሩ ግብጻውያን ስጋት ነውን?