በቄለም ወለጋ ታጣቂዎች የኤሌክትሪክ መስመር ላይ በፈጸሙት ጥቃት መብራትና ውሃ ከተቋረጠ አንድ ወር አለፈው

በቄለም ወለጋ ዘጠኝ ወረዳዎች ውሃና መብራት ከተቋረጠ አንድ ወር እንዳለፈው ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Godong

የቄለም ወለጋ ደምቢዶሎን ጨምሮ በዘጠኝ የዞኑ ወረዳዎች የመብራት እና የውሃ አገልግሎት ከተቋረጠ ከአንድ ወር በላይ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ለቢቢሲ አስታወቀ።

በዞኑ የመብራት አገልግሎት የተቋረጠው ከደምቢዶሎ ወደ ጋምቤላ የተዘረጋው የኤሌትሪክ መስመር አንፊሎ የሚባል ቦታ ላይ በጠዓታቂዎች በመቋረጡ እና የኤሌትሪክ ተሸካሚ ምሰሶዎች ጉዳት ስለደረሰባቸው መሆኑን የዞኑ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሃምባ ረጋ ተናግረዋል።

የዞኑ ዋና ከተማ የሆነችውን ደምቢዶሎን ጨምሮ ሰዩ፣ ጅማ ሆሮ፣ ጋዎ ቄቤ፣ ያማ ሎጊ ወለል የሚባሉ ወረዳዎች የኤሌትሪክ ኃይል መቋረጥ ካጋጠማቸው መካከል ይጠቀሳሉ።

ከዚህ በተጨማሪ የአብዛኛው የዞኑ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ከመብራት ኃይል ጋር የተገናኘ በመሆኑ ደምቢዶሎን ጨምሮ በዘጠኝ ወረዳዎች ውሃም ከተቋረጠ ከወር በላይ መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የደምቢዶሎ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ባለፈው አንድ ወር ከአካባቢያቸው ርቀው በመሄድ ውሃ ከወንዝ እየቀዱ እነደሚጠቀሙ፣ ሌሎቹ ደግሞ የዝናብ ውሃ እያጠራቀሙ እንደሚገለገሉ ተናግረዋል።

እህል ለማስፈጨት ራቅ ብሎ ያለ በነዳጅ የሚሰራ ወፍጮ ቤት በመሄድ እንደሚያስፈጩ የተናገሩት አንድ የደምቢዶሎ ነዋሪ፣ "ከባድ ችግር ውስጥ ነው ያለነው፤ የምንበላውን ልናጣ እንችላለን" ሲሉ ስጋታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የችግሩ መነሻ ምንድን ነው?

ከደምቢዶሎ ወደ ጋምቤላ ኤሌትሪክ ለማስተላለፍ የተዘረጋው መስመር የተቋረጠው በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መሆኑን የዞኑ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

"የተቆረጠውን መስመር ለመጠገን መንግሥት ባለሙያዎች ወደ ስፍራው ልኮ ነበር። ነገር ግን ታጣቂዎቹ የሚጠቀሙባቸውን ሁለት መኪኖች አቃጥለውባቸው እነርሱንም ለሦስት ቀናት አግተው ከደበደብዋቸው በኋላ በአራተኛው ቀን ለቅቀዋቸዋል" ይላሉ ኃላፊው።

በኦነግ ሸኔ ታግተው የነበሩት የኤሌትሪክ ኃይል ባለሙያዎች ሰባት ሲሆኑ የተቃጠሉት መኪኖች ደግሞ የዞኑ ቅርንጫፍ ቢሮ መኪኖች የሆኑ አንድ ፒክ አፕና አንድ አይሱዙ መሆናቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

ይህ ድርጊት የተፈፀመው ባለፈው ሳምንት መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው ባለሙያዎቹ ጥቃቱ ያጋጠማቸው አንፊሎ ወረዳ ዳዎ ቶፒና ያሬድ የሚባል አካባቢ መካከል መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህ ባለሙያዎች መታገታቸውን ተከትሎ የመንግሥት የፀጥታ አካላት ክትትል እያደረጉ የነበረ ቢሆንም፣ በአራተኛው ቀን ታጣቂዎቹ እንደለቀቋቸው ይናገራሉ።

" ባለሙያዎቹ አሁን ተደብቀው ነው ያሉት፤ እነርሱን አግኝተን የጥገናው ሥራ እንዲቀጥል ማድረግ አልቻልንም" የሚሉት ኃላፊው፣ በዞን አስተዳደሩ በኩል የተቋረጠውን መብራት የማስቀጠል ዝግጁነት መኖሩን ገልፀዋል።

ኃላፊው አክለውም ባለሙያዎቹን ስላላገኘን የጥገናውን ስራ አልጀመርንም ሲሉ ያለውን ሁኔታ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በተጨማሪም አሁንም እንደ ጊዳሚ እና አንፊሎ ባሉ የዞኑ ወረዳዎች የፀጥታ ችግር መኖሩን የዞኑ ኃላፊ ይናገራሉ።

በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ አራት ዞኖች በተለይም በምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች ውስጥ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች በነዋሪዎች: በአካባቢ ባለስልጣናትና በፀጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ እንደሆነ ሲነገር መቆየቱ ይታወቃል።

ይህ ታጣቂ ቡድን በመንግሥት ኃላፊዎች እና በንፁኀን ዜጎች ግድያ በተደጋጋሚ ይወነጀላል።