በግብጽ በኮሮናቫይረስ የሞተችን ሴት ከተቀበረችበት ቆፍረው አስከሬኗን አቃጠሉ

መቃብር የሚቆፍር ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, KHALED DESOUKI

የግብጽ ባለስልጣናት በኮሮናቫይረስ የሞተችን ሴት ከተቀበረችበት ቆፍረው አስከሬኗን ያቃጠሉ ግለሰቦች ላይ ምርመራ እንደከፈቱ አስታውቀዋል።

የአገሪቱ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ከመቃብር ተቆፍሮ አስከሬኗ የተቃጠለው ግለሰብ የሆስፒታል ነርስ መሆኗን ነው። ነርሷ በኮሮናቫይረስ የሞተችው በደቡብ ካይሮ በምትገኘው ሄልዋን ግዛት ነው።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በግብፅ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ መገለልና አድልዎን እያደረሰ ነው ተብሏል። በቫይረሱ የተያዙ ህሙማን መገለልን ጨምሮ ሌሎች ነገሮችን እንደሚያስተናግዱም እየተዘገበ ነው።

በአንዳንድ አጋጣሚዎችም በኮሮናቫይረስ ህመም የሞቱ ግለሰቦች በማህበረሰቡ የመቃብር ቦታ እንዳይቀበሩ የሚከለክሉ እንዳሉም ሪፖርት ተደርጓል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተባት ዕለት ጀምሮ ግብጽ 206 ሺህ 510 የኮሮናቫይረስ ህሙማንን የመዘገበች ሲሆን 12 ሺህ 253 ዜጎቿንም በቫይረሱ ማጣቷን መረጃዎች ያሳያሉ።