የፓሪስ መቆሸሽ ተቃውሞን ቀሰቀሰ

የፓሪስ ቆሻሻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ውቧ ከተማ ፓሪስ መንገዶቿ ተቆፋፍረዋል፣ ቆሻሻ ሞልቷቸዋል ያሉ ዜጎች በኦንላይን ላይ ተቃውሞ ቀስቅሰዋል፡፡

ተቃዋሚዎቹ የጀመሩት ይህ ተቃውሞ ቆሻሻ መንገዶችንና በጊዜ ያልተነሱ የቆሻሻ ገንዳዎችን ፎቶ እያነሱ በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች የማጋለጥ ተግባር ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘቱ ሺዎች ተቀላቅለውታል፡፡

የሚጋሩት ፎቶዎችም በማኅበራዊ ሚዲያ እንደ ሰደድ እሳት ተዛምተዋል፡፡

የፓሪስ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ይህ ‹‹ስምን የማጠልሸት ፖለቲካዊ ዘመቻ›› እንጂ ሌላ አይደለም ብለዋል፡፡

‹ቆሻሺት ፓሪስ› የሚል የዘመቻ የወል ስም በመክፈት ያልተጠገኑ ጎዳናዎችንና ያልተነሱ ቆሻሻዎችን ፎቶ በማንሳት የማጋለጡን ቅስቀሳ ማን እንደጀመረው አይታወቅም፡፡

ሆኖም ዘመቻው በተለይም በፈረንጆች ፋሲካ አካባቢ ተዛምቶ ሰንብቷል፡፡

የፓሪስ ምክትል ከንቲባ ዘመቻውን ፖለቲካዊ ብለውታል፡፡

ፓሪስን ማጽዳት ቀላል ሥራ እንዳልሆነ የጠቀሱት ምክትል ከንቲባው ፓሪስ ሚሊዮኖች እጅግ በተጣበበ ሥፍራ የሚኖሩባት ውብ ከተማ እንደሆነች መዘንጋት የለበትም ብለዋል፡፡

ዘመቻውን በትዊተር የተቀላቀለ አንድ ነዋሪ ፓሪስ ለዓመታት ብርሃናማዋና ውቧ የዓለም ከተማ ከሚለው ስሟ ጋር የሚመጥን ጽዳት እንደሌላት ጠቅሶ ለዚህም ከንቲባ አን ሂዳልጎን ተጠያቂ አድርጓል፡፡

የቀኝ አክራሪዋ ፖለቲከኛ መሪን ሌፔን ይህን የተቃውሞ ዘመቻ የተቀላቀለች ሲሆን በትዊተር ሰሌዳዋ ‹የፓሪስን ቆሻሻ ክምር ማየት ለፓሪሳዊያን ልብ የሚሰብር ነው› ስትል ፅፋለች፡፡

ምክትል ከንቲባው በሰጡት ምላሽ ‹አንድ ሰው የቀኑን አስቀያሚ አጋጣሚ ብቻ ፎቶ ቢያነሳ የሰውየው ሕይወት አስቀያሚ ነው ብለን መደምደም የለብንን፡፡ እውነታውን ለማየት አይናችንን እንግለጥ› ሲሉ ዘመቻው የከተማዋን መጥፎ ገጽታ ብቻ የማጉላት እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

ፓሪስ ከ2 ሚሊዮን ሰዎች በላይ በ10 ኪሎ ሜትር ባልራቀ ዙርያ ገብ የሚኖሩባት በየዓመቱ ከ30 ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎች የሚያዘወትሯት ከተማ ናት፡፡