ኮሮናቫይረስ፡ የአሜሪካ መንግሥት የክትባት ፓስፖርት ሃሳብን ውድቅ አደረገ

እየተከተበች ያለች ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ መንግሥት የኮቪድ-19ኝን ክትባት የወሰዱ ሰዎችን ለመለየት የሚያስችለውን የጉዞ ሰነድ የማስተዋወቅን ሃሳብ ‹‹የግል ሚስጥሮች እና ሌሎች መብቶች ሊጠበቁ ይገባል›› በሚል ሃሳቡን ውድቅ አድርጎታል፡፡

ይህንን አዲስ አይነት የጉዞ ሰነድ የማዘጋጀት ሃሳብ በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በመላው አለም የተጓዦችን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል እየታሰበበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን የሃሳቡ ተቃዋሚዎች የሰዎችን የእኩልነት መብት ሊያሳጣ ይችላል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

እስካሁን ድረስ 550 ሺህ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ያጣችው የአሜሪካ መንግስት ዜጎቹ ሰነድ ይዘው እንዲጓዙ የሚያስገድድ ስርአት እንደማይደግፍም ይፋ አድርጓል፡፡

የዋይት ሃውሷ ቃል አቀባይ ጄን ፕሳኪ የኮሮና ቫይረስ ክትባት የወሰዱ ሰዎችን ማነንት የሚመዘገብ የመረጃ ቋት እንደማይደራጅም ተናግረዋል፡፡

አክለውም ‹‹ የኮሮና ቫይረስ ክትባት የወሰዱ ሰዎች አንድም የምስክር ወረቀት እንዲይዙ የሚያስገድድ ትዕዛዝ የፌደራል መንግስቱ አያወጣም›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

‹‹መንግስት አሁንም ሆነ ወደፊት አሜሪካዊያን የምስክር ወረቀት እንዲይዙ የሚያስገድድ ስርዐትን አይደግፍም›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በአለም ላይ ካሉ አገራት እንግሊዝ ‹‹የኮሮናቫይረስ ሁኔታ የምስክር ወረቀት›› የተሰኘ ስርአትን በማበልፀግ ላይ ስትሆን ይህም የሙዚቃ ድግሶችን እና የስፖርት ግጥሚየዎች እንዲካሄዱ የሚያስችል ይሆናል ተብሏል፡፡ ስርአቱ የኮሮና ቫይረስ ክትባት የወሰዱ ሰዎችን ወይም ከበሽታው ያገገሙ ሰዎችን ለመለየት እና ለመመዝገብ ያስችላል ተብሏል፡፡

የአውሮፓ ህብረትም ተመሳሳይ ሰነዶችን ለማስተዋወቅ እየሰራ ሲሆን እስራኤል በበኩሏ ‹‹ አረጓንዴ ካርድ›› የተሰኘ እና ሙሉ በሙሉ የተከተቡ ሰዎች ወይም ከኮሮና ቫይረስ ያገገሙ ሰዎች የሚይዙትን ካርድ መስጠት ጀምራለች፡፡ ይህም ዜጎቿ ሆቴሎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ወይም ቴያትሮች ሲሄዱ የሚያሳዩት ካርድ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የአለም የጤና ድርጅት በበኩሉ በአሁኑ ወቅት የክትባት ፓስፖርትን የመያዝ ሃሳብን እንደማይደግፍ እና ይህም ገና ክትባቱ የቫይረሱን ስርጭት ይቀንስ አይቀንስ ሳይታወቅ ብሎም የእኩልነት መብቶቸን እንዳይጋፋ በሚል ነው፡፡