የአውሮፓ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስገዳጅ የህፃናት ክትባትን ደገፈ

ህፃን ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ቼክ ሪፐብሊክ ለህፃናት አስገዳጅ ብላ ላቀረበችው የህፃናት ክትባት ፖሊሲ ድጋፍ ሰጥቷል።

ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤቱ የወሰዱት ልጆቻቸውን አናስከትብም ያሉ የአፀደ ህፃናት ወላጆች ናቸው።

እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸውን ባለማስከተባቸው ትምህርት ቤት አይገቡም የሚል ክልከላን እንዲሁም ቅጣትን አስተናግደዋል ተብሏል።

ወሳኝ በተባለው በዚህ ፍርድ ቤት ብያኔ ምንም እንኳን ቼክ ያወጣችው ፖሊሲ የግል ህይወት ላይ ጣልቃ የሚገባ ቢሆንም የማኅበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ ግን መሠረታዊነቱ ታምኖበታል ተብሏል።

ወላጆቹ የክሳቸው መነሻ የነበረው ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት ነው።

ነገር ግን የህፃናት ክትባት ጉዳይ አወዛጋቢ የሆነው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ነው።

የህፃናት በሽታዎችን ለመከላከል ክትባት አስገዳጅ እንዲሆን ውሳኔ ሲወስን የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ፍርድ ቤቱ የቼክ ሪፐብሊክን ፖሊሲ 16 ለ 1 በሆነ ድምጽ ድጋፍ ሰጥቶታል።

"ለዲሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ እነዚህ እርምጃዎች አስፈላጊ ናቸው" በማለት ፍርድ ቤቱ ያሳወቀ ሲሆን አክሎም "ህፃናት ከከፉ በሽታዎች በክትባት ወይም ደግሞ አቅማቸውን በማዳበር ሊጠበቁ ይገባል" ብሏል።

በቼክ ሪፐብሊክ ሕግ መሰረት ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ከተለያዩ በሽታዎች እንዲጠበቁ ለማድረግ ማስከተብ ግዴታ ነው። ክትባት ሊቀር የሚችለው ህፃናቱ በተለያዩ የጤና እክሎች ምክንያት መከተብ ሳይችሉ ሲቀሩ ነው።

ምንም እንኳን አገሪቷ አስገዳጅ ሕግ ብታስቀምጥም ህፃናቱን አስገድዳ ክትባት አትከትብም፤ እንዲሁም ልጆቹ ካደጉ በኋላም ክትባት ባለመከተባቸው ትምህርት ቤት እንዳይገቡ አትከለክልም።

ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ከቀረቡት ክሶች መካከል ልጃቸው ኩፍኝን ጨምሮ ጆሮ ደግፍና ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል የሚሰጠውን ክትባት አናስከትብም በማለታቸው ትምህርት ቤቱ አንቀበልም ብሏቸዋል።