በኮሮና የተያዙ ሰዎች በድባቴ እና የመርሳት በሽታ የመጠቃት እድላቸው እንደሚጨምር ጥናት አመለከተ

ታካሚ በሆስፒታል ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፈው ስድስት ወራት ውስጥ የኮሮናቫይረስ የያዛቸው ሰዎች በድባቴ፣ የመርሳት በሽታ፣ ስትሮክ እና በሳይኮሲስ ህመሞች የመጠቃት እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን በኦክስፎርድ ተመራማሪዎች የተሰራ ጥናት አመላከተ።

ከእነዚህ ውስጥ አንድ ሶስተኛው ቀድመው የነበሩባቸው የስነ ልቦና እና የነርቭ ችግሮች ያገረሽባቸዋል ወይም እንደ አዲስ ሕመሞቹ ያጠቋቸዋል ሲል ጥናቱ አመልክቷል።

በቫይረሱ ተይዘው ሆስፒታል የገቡ ወይም በፅኑ ህሙማን ማቆያ ከነበሩ ደግሞ የመያዝ እድላቸው የበለጠ ይሰፋል ሲል ጥናቱ አመላክቷል።

እነዚህ ጫናዎችም ጭንቀትን በማስከተል ወይም ቫይረሱ አዕምሮ ላይ በሚያስከትለው ቀጥተኛ ጫና ላይ ሊመሰረት እንደሚችልም አክሏል።

እንግሊዛዊያን ሳይንቲስቶቹ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ በአሜሪካ የኮሮናቫይረስ ተጠቂዎችን የኤሌክትሮኒክ መረጃ በመመልከት እና በተለይም 14 ለሚሆኑ የስነ-ልቦና እና የነርቭ ችግሮች የመጋለጥ እድሎችን መርምረዋል።

ከእነዚህም መካከል የአዕምሮ ውስጥ የደም መፍሰስ፣ ስትሮክ፣ ፓርኪንሰን፣ የመርሳት በሽታ፣ ሳይኮሲስ፣ የስሜት መቃወስ እና የጭንቀት ችግሮች ይገኙበታል፡፡

በጣም መታመምን ወይም ወደ ሆስፒታል መወሰድ ከሚያስከትለው የጭንቀት ጫና የተነሳ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ለጭንቀት እና የስሜት መቃወስ መዳረግ በተደጋጋሚ የታዩባቸው ችግሮች ናቸው ሲል ገልጿል።

እንደ ስትሮክ እና የመርሳት በሽታ ያሉት ደግሞ ቫይረሱ በራሱ በሚያስከትለው አካላዊ ጉዳት ላይ ተመስርተው የሚከሰቱ ወይም ሰውነታችን ለቫይረሱ በሚሰጠው ምላሽ ምክንያት ሊከሰቱ ይችላሉ ሲልም አስረድቷል።

ጥናቱ የኮሮናቫይረስ በቀጥታ ለፓርኪንሰን ወይም ለጊላይን-ባሬ ሲንድሮም የማጋለጥ እድሉን አላረጋገጠም።

ምርምሩ ሁለት በጉንፋን የተያዙ ሰዎችን የያዙ ቡድኖችን በኮሮናቫይረስ ከተያዙት ጋር በማነፃፀር የተሰራ ሲሆን፣ ጥናቱን ያካሄዱት የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ኮሮና ከሌሎች የመተንፈሻ ህመሞች በበለጠ ከአዕምሮ ጉዳቶች ጋር እንደሚያያዝ ገልፀዋል።

ቫይረሱ ወደ አዕምሮ ውስጥ እንደሚገባ እና ጉዳቶችን እንደሚያደርስ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ተገኝተዋል ሲሉ ከተመራማሪዎቹ አንዱ የሆኑት የኦክስፎርዱ የኑሮሎጂ ፕሮፌሰር መሱድ ሃሰን አብራርተዋል፡፡

ከቀጥተኛ ጉዳቶችም ባሻገር የደም መርጋትን በማስከተሉ እና ይህም ስትሮክን ሊያመጣ እንደሚችል አክለዋል፡፡ በአጠቃላይም ሰውነታችን ቫይረሱን ለመከላከል ሲል የሚያደርገው ግብ ግብ አእምሮን ሊጎዳ ይችላል ሲሉም ገልፀዋል፡፡