ኮሮረናቫይረስ፡ ጃፓናዊቷ የኮቪድ-19 ታማሚ በህይወት ካለ ሰው የሳንባ ንቅለ ተከላ በማድረግ የመጀመሪያ ሆነች

የደረት ራጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ኮሮናቫይረስ በሳንባ ላይ ከባድ ጉዳትን ያደርሳል

አንዲት የኮቪድ-19 ታማሚ ጃፓናዊት በህይወት ካሉ ሰዎች ሳንባ በመቀበል በዓለማችን የመጀመሪያዋ የኮሮናቫይረስ ህመምተኛ ለመሆን በቃች።

ግለሰቧ በቀዶ ህክምና በአካሏ ላይ እንዲገባ የተደረገውን የሳንባ ክፍል ከልጇና ከባሏ የተበረከተ ነው ተብሏል።

ታማሚዋ ሳንባው የተለገሳት በኮሮናቫይረስ ምክንያት የመተንፈሻ አካሏ እንደ አንድ የሰውነት ክፍሏ መደበኛውን ሥራውን መሥራት በማቆሙ ነው።

በኪዮቶ የሚገኙ ሐኪሞች እንዳሉት ሴትየዋ በቅርብ ወራት ውስጥ አገግማ ወደ ሙሉ ጤናዋ ትመለሳለች።

ጃፓን ውስጥ ከሞቱ ሰዎች ላይ የሚገኝን የሳንባ ልገሳ ለማግኘት ያለው ወረፋ ብዙ ጊዜን መጠበቅን ይጠይቃል። በሕይወት ካሉ ሰዎች ሳንባ ንቅለ ተከላ ለኮቪድ-19 በሽተኛ ሲለገስ ግን ይህ የመጀመሪያው ነው።

ንቅለ ተከላው የተደረገበት የኪዮቶ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል የሳንባ መተካቱን ሂደት 11 ሰዓታት በፈጀ የቀዶ ህክምና ሂደት አጠናቆታል።

ሐኪሞቹ እንዳሉት ሳንባውን የለገሱት ባልና ልጅ እንዲሁም ሳንባ የተለገሳት ታማሚ ሦስቱም በመልካም የጤንነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።

በቻይና፣ በአውሮፓና በአሜሪካ በተመሳሳይ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሳንባቸው ከጥቅም ውጪ የሆነባቸው ታማሚዎች የሞቱ ሰዎችን ሳንባ በመቀበል እየዳኑ ይገኛሉ።

ነገር ግን ከሞቱ ሰዎች ሳንባ ማግኘት ተራን የመጠበቁ ሂደት በጃፓን ዓመታትን የሚወስድ ነው።

ሌላ ተያያዥ በሽታ ያልነበረባት ይህች ጃፓናዊት ታካሚ ኮቪድ-19 ከተያዘች በኋላ በሕይወት ለመቆየት የግድ የሳንባ ንቅለ ተከላ እንደሚያስፈልጋት ከታወቀ በኋላ ባሏና ልጇ ይህን ልገሳ ለማድረግ አላቅማሙም።

በሕይወት ከሚገኘው ልጇና ከባለቤቷ ለግለሰቧ የተሰጠው የተወሰነ የሳንባ ክፍላቸው ነው።

የሚቀራቸው ሳንባ አነስተኛ በመሆኑ ሊፈጥርባቸው የሚችለው የጤና እክል ልገሳውን ከማድረጋቸው በፊት ተብራርቶላቸዋል።

ንቅለ ተከላውን የመሩት ፕሮፌሰር ለጃፓኑ ኪዮዶ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ይህ በሕይወት ካሉ ሰዎች ሳንባን ወስዶ ለሌላ ሰው የመትከል ሂደት ትልቅ የሕክምና አምርታ ነው ብለዋል።