የንግሥት ኤልዛቤት ባለቤት ልዑል ፊሊፕ በ99 ዓመታቸው አረፉ

ልዑል ፍሊፕ

ልዑል ፊሊፕ፣ በ99 ዓመታቸው ማረፋቸውን የባኪንግሃም ቤተመንግሥት አስታወቀ።

ልዑሉ የንግሥት ኤልዛቤት ባለቤት ሲሆኑ፣ ከልዕልቷ ጋር የተጋቡት ንግሥት ከመሆናቸው አምስት ዓመታት በፊት በ1947 (እአአ) ነበር። ንግሥቲቱ በብሪታኒያ የነገሥታት ታሪክ ረጅም ጊዜ በንግሥና የቆዩ ናቸው።

ከባኪንግሐም ቤተ መንግሥት የወጣው መግለጫ እንዳለው "ግርማዊት ንግሥት ኤልዛቤት በጥልቅ ሐዘን የተወዳጁን ባለቤታቸውን የኤደንብራው ልዑል ፊሊፕን ሞት ይፋ አድርገዋል።

"ክቡርነታቸው በዊንድሰር ቤተመንግሥት ውስጥ ዛሬ ጠዋት አርፈዋል" ብሏል።

ባለፈው መጋቢት ወር ላይ የኤደንብራው አልጋ ወራሽ ልዑል ፊሊፕ ለአንድ ወር ያህል ህክምና ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ ከሆስፒታል መውጣታቸው ይታወሳል።

ልዑሉ ቀደም ሲል ለነበረባቸው የልብ ችግር ለንደን ውስጥ በሚገኘው ሴንት ባርቶሎሚው ሆስፒታል ውስጥ ቀዶ ጥገና ተደርጎላቸው ነበር።

ልዑሉና ንግሥቲቱ በዘመናቸው አራት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን ስምንት የልጅ ልጆችና አስር የልጅ፣ ልጅ ልጆችን አይተዋል።

የመጀመሪያ ልጃቸው የዌልሱ ልዑል፣ ልዑል ቻርለስ በ1948 (እአአ)፣ ተከታይ እህታቸው ልዕልት አን በ1950፣ የዮርኩ አልጋ ወራሽ ልዑል አንድሩ በ1960 እና ልዑል ኤድዋርድ ደግሞ በ1964 ነበር የተወለዱት።

ልዑል ፊሊፕ በግሪኳ ደሴት ኮርፉ ውስጥ እንደ አውሮፓውያኑ ሰኔ 10/1921 ነበር የተወለዱት።

የልዑሉ አባት የሄለኒስ ንጉሥ ቀዳማዊ ጆርጅ የመጨረሻ ልጅ የነበሩት የግሪክና የዴንማርክ ልዑል አንድሩ ነበሩ።

እናታቸው ልዕልት አሊስ የሎርድ ልዊስ ሞንትባተን ሴት ልጅ እና የንግሥት ቪክቶሪያ የልጅ ልጅ ነበሩ።

የልዑሉን ሞት ተከትሎ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን "የበርካታ ወጣቶችን ሕይወት ያነቃቁ ነበሩ" ሲሉ ሐዘናቸውን ከጽህፈት ቤታቸው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም "ንጉሣውያን ቤተሰቡን እንዲሁም ዘወዳዊውን ሥርዓት የሚመሩ በመሆናቸው ተቋሙ ያለምንም መዛነፍ በብሔራዊ ሕይወታችን ላይ አስፈላጊ እንዲሆን አድርገዋል።"

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም የኤደንብራውን ልዑል ሞት "በጥልቅ ሐዘን ውስጥ" ሆነው መስማታቸውን ተናግረዋል።

"ልዑል ፊሊፕ በዩናይትድ ኪንግደምም ሆነ በኮመንዌልዝ አገራት እንዲሁም በመላው ዓለም የትውልዶችን ፍቅር ያገኙ ናቸው" ብለዋል።

ልዑል ፊሊፕ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት የተሳተፉና በሕይወት ከነበሩ ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ መሆናቸውንም አስታውሰዋል።

የልዑል ፊሊፕ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዊንድሰር ውስጥ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚፈጸም ሲሆን፤ ነገር ግን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሥነ ሥርዓቱ ዝግጅት ላይ ማስተካከያ እንደተደረገ ተገልጿል።

የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ከሚያስፈጽመው አካል በወጣው መግለጫ መሰረት ከሥርዓተ ቀብሩ በፊት "ከዚህ በፊት እንደ ነበረው ልማድና እንደ የልዑሉን ፍላጎት መሠረት በማድረግ" አስከሬናቸው ዊንድሰር ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚቆይ ይሆናል።

መግለጫው እንዳለው "በኮቪድ-19 ምክንያት የቀብር ሥነ ሥርዓቱ የሚካሄድበት ሁኔታ ላይ ማስተካከያ በመደረጉ፤ ሕዝቡ በቀብሩ ላይ ለመገኘትም ሆነ ተሳታፊ ለመሆን ሙከራ እንዳያደርግ እንጠይቃለን" ብሏል።