ልዑል ፊሊፕ፡ የዓለም መሪዎች በልዑል ፊሊፕ ሞት ኃዘናቸውን እየገለፁ ነው

ባራክ ኦባማ ከእንግሊዝ ንጉሳውያን ቤተሰቦች ጋር

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የተለያዩ አገራት መሪዎችና ባለስልጣናት በ99 አመታቸው ህይወታቸው ላለፈው የኤድንብራው መስፍን ልዑል ፊሊፕ የተሰማቸውን ኃዘን እየገለፁ ነው።

የአውሮፓ ንጉሣውያን ድርጅት እንዲሁም ኮመንዌልዝ ተብለው የሚጠሩት አገራት መሪዎች የኤድንብራው መስፍን ለአገራቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦ ትልቅ ምስጋናን በመቸር አወድሰዋቸዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ልዑል ፊሊፕን "ድንቅ ሰው" በማለት ያወደሷቸው ሲሆን በህይወት ያሉት የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች በሙሉ የኃዘን መግለጫ አስተላልፈዋል።

የልዑሉን ህይወት ለመዘከር በሚል የማስታወሻ ስነ ስርዓት በዛሬው እለት እንግሊዝ በሚገኝ አንድ ቤተ ክርስቲያን ይፈፀማል። በአውስትራሊያዋ ሲድኒም እንዲሁ በቤተ ክርስቲያን የልዑሉ ህይወት የተዘከረበት አገልግሎት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዑሉን " ቁርጠኛ፤ ሁሉም የሚተማመንባቸው እንዲሁም ከንግሥቲቷ ጎን ያልተለዩ" በማለት አሞካሽተተዋቸዋል።

በቅዱስ አንድሪው ካቴድራል በተፈፀመው ስነ ስርዓት ላይ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች የተገኙ ሲሆን ለንጉሳውያን ቤተሰቦች የፀሎት ስነ ስርዓት ተደርጓል እንዲሁም ልዑል ፊሊፕንም በዚህ ወቅት አክብረውታል።

"ልዑል ፊሊፕ በርካታ ጊዜ አውስትራሊያን ጎብኝተዋል። በነዚህ ወቅቶችም ልዑሉ ለሰው አዛኝ፣ ሰው ወዳድ፣ ቸር መንፈስ ያላቸውና ጠያቂ መሆናቸውን ተገንዝበናል" በማለት በቤተክርስቲያኑ ስርዓት ላይ ቄስ ሬቨረንድ ካኒሽካ ደ ሲልቫ ራፌል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አክለውም የሳቸው ሞት ማህበረሰቡን "ጥልቅ ኃዘን ውስጥ አስገብቶታል" ብለዋል።

በጎረቤት አገር ኒውዚላንድ በመዲናዋ ዌሊንግተን ለክብራቸው ሲባል 41 ጥይት ዛሬ እኩለ ቀን ላይ ይተኮሳል።

የሮማው ካቶሊክ ፖፕ ፍራንሲስ ልዑሉ ለቤተሰብና ለጋብቻ የነበራቸውን ጠንካራ አመለካከት በመጥቀስ ኃዘናቸውን ገልፀዋል።

የቲቤቱ መንፈሳዊ መሪ ዳላይ ላማ ለንግሥቲቷ ደብዳቤ የፃፉ ሲሆን ልዑሉ ትርጉም ያለው ህይወት በመኖራቸው ይታወሳሉ ብለዋል።

የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ሺንፒንግም የኃዘን መግለጫ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።