ኮሮናቫይረስ ፡ህንድ እስከ መጪው ሃምሌ 250 ሚሊዮን ህዝብ እከትባለሁ አለች

ከ60 አመት በላይ የሆናቸው ህንዳውያን

የፎቶው ባለመብት, EPA

ህንድ እስከ መጪው ሃምሌ 250 ሚሊዮን ህዝቧን የኮሮናቫይረስ መከላከያ የመክተብ እቅድ እንዳላት አስታውቃለች።

ለዚህም የሚሆን 500 ሚሊዮን መጠን (ዶዝ) ክትባት በዝግጅት ላይ እንደሆነም መንግሥት ከሰሞኑ አስታውቋል።

አገሪቷ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ ያለቻቸውን የማህበረሰብ ክፍል በከፍተኛ ፍጥነት እየከተበች ሲሆን እስካሁንም ድረስ ከ100 ሚሊዮን መጠን (ዶዝ) ያለው ክትባት ተከፋፍሎ መድረሱን አስታውቃለች።

በሁለተኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ በተመታችው ህንድ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በየቀኑ በአማካኝ የምትመዘግበው የቫይረሱ ታማሚ ቁጥር ከ90 ሺህ በላይ ሆኗል ተብሏል።

ከወረርሽኙ ጋር በመታገል ጎን ለጎን ክትባት እየከተበች ሲሆን ከ45 አመት በላይ የሆኑ ሰዎች በሙሉ መከተብ እንደሚችሉ ተገልጿል።

ክትባቶቹንም ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ ማዕከላትና ሆስፒታሎች በቀላሉ ማግኘት ይቻላል።

እስካሁን ድረስ በከፍተኛ ደረጃ የተከተቡት ከ60 አመት በላይ የሆናቸው የእድሜ ባለፀጎችና የጤና ባለሙያዎች ናቸው።

በአለም ላይ ካሉ አገራት 100 ሚሊዮን መጠን ያለው ክትባት በማዳረስ ቀዳሚዋ አገር ህንድ ስትሆን ይህንንም ለማድረግ የፈጀባት 85 ቀናት መሆኑን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

አሜሪካ ይህንን ያህል መጠን ከመክተብ 89 ቀናት የፈጀባት ሲሆን ቻይና ደግሞ 102 ቀናት መውሰዱን የጤና ሚኒስቴሩ አክሎ ገልጿል።

ምንም እንኳን አገሪቷ በከፍተኛ መጠን እየከተበች ቢሆን በዚሁ ሳምንት በርካታ ግዛቶች የክትባት እጥረት እንዳጋጠማቸው ሪፖርት አድርገዋል።

ሆኖም የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ክምችት አለኝ፤ እጥረት የሚለው መሰረት የሌለው ነው ብሏል። ከ40 ሚሊዮን መጠን በላይ ክትባት በማከማቻዬ ውስጥ አለኝ ብሏል።

ሆኖም አገሪቷ እስከ መጪው ሃምሌ ድረስ 250 ሚሊዮን ዜጎቿን ለመክተብ የምታቅድ ከሆነ ፍጥነቷን ልትጨምር እንደሚገባ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ወረርሽኙ ከተነሳ ጀምሮ 12 ሚሊዮን ሰዎች በኮሮናቫይረስ የታዩዙባት ህንድ 167 ሺህ ዜጎቿንም በሞት ተነጥቃለች።