ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ሃብታም አገራት ለክትባት ያሳዩትን ስግብግብነት ተቹ

በኮቫክስ በኩል ለደሃ አገራት የሚቀርብ የክትባት ጭነት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

በኮቫክስ በኩል ለደሃ አገራት የሚቀርብ የክትባት ጭነት

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በድሃና ሃብታም አገራት ውስጥ ያለውን የኮሮናቫይረስ ክትባት አቅርቦት ፍትሐዊ አለመሆን አሳፋሪ እንደሆነ ተናገሩ።

ዳይሬክተሩ እንደገለጹት በሁሉም አገራት ክትባቱ ተዳርሶ ለማየት የነበረው የረዥም ጊዜ ዕቅድ ሳይሳካ መቅረቱን አውስተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 ክትባትን በፍትሐዊነት ለድሃና ሃብታም አገራት በእኩል ለማዳረስ በአያሌው ሲታትር ነበር።

ይህንኑ ዕቅዱን እውን ለማድረግም ኮቫክስ የተሰኘ ፕሮጀክት ዘርግቶ ሰፊ የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ ነበር።

ኮቫክስ ለድሃ አገራት ክትባቱን ለማዳረስ የተቋቋመ የአገራት ጥምረት ነው።

እስከ አሁን ለ100 ድሃ አገራት 38 ሚሊዮን ብልቃጥ ክትባቶችን ማደረስ ችሏል። ሆኖም ይህ ከዕቅዱ በታች ነው።

ኮቫክስ ሲቋቋም ዕቅዱ የነበረው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለ190 አገራት 2 ቢሊዮን ብልቃጦችን ማድረስ ነበር።

92 ድሃ አገራት ልክ ሃብታም አገሮች ያላቸውን የክትባት አቅርቦት በተመሳሳይ ጊዜ እንዲያገኙ ለማስቻልም እየሰራ ነበር። ሆኖም ኮቫክስ ይህ ዕቅዱ ተፋርሶበታል።

"በድሃና ሃብታም አገራት መካከል ያለው ልዩነት አስደንጋጭ ነው" ብለዋል ዶ/ር ቴድሮስ ትናንት አርብ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ።

"በአማካይ ከሃብታም አገራት ከ4 ሰው አንዱ ክትባቱ ደርሶታል። በድሃ አገራት ግን ከ500 ሰዎች አንዱ ብቻ ነው ክትባቱ የደረሰው" ሲሉ የኢፍትሐዊነቱን ምጣኔ አብራርተዋል።

ኮቫክስ እንደ እቅዱ ቢሆን ኖሮ በመጋቢት መጨረሻ 100 ሚሊዮን ብልቃጦችን ለድሃ አገራት ማድረስ ነበር። አሁን ማሳካት የቻለው ግን 38 ሚሊዮኑን ብቻ ነው።

ዶ/ር ቴድሮስ በመጋቢት መጨረሻ የነበረውን እቅድ በሚያዝያ ወይም ግንቦት ለማሳካት እየተፍጨረጨርን ነው ብለዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ አንዳንድ አገራት ኮቫክስን ቸል ብለው የቀጥታ የሁለትዮሽ ስምምነት እያደረጉ አግኝተናቸዋል ያሉ ሲሆን፤ ይህንንም የሚያደርጉት የንግድና የፖለቲካ ትርፍን አስልተው ነው ሲሉ አምርረው ተችተዋቸዋል።

ይህ የሁለትዮሽ ስምምነት በድሃና ሃብታም አገራት የሚኖረውን የክትባት አቅርቦት መመጣጠን ጨርሶውኑ እንዲፋለስ ያደርገዋልም ብለዋል።

በዚህ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መባቻ ዶ/ር ቴድሮስ የሃብታም አገራትን ስግብግብነትና ራስ ወዳድነትን ክፉኛ ወቅሰው እንደነበረ ይታወሳል።

"ለኔ ብቻ የሚለው አስተሳሰብ መልሶ ራሰን የሚጎዳ ነው፤ ምክንያቱም ለኔ ብቻ ብሎ ክትባቱን ማከማቸት ወረርሽኙን መጋዘን ውስጥ የማከማቸት ያህል ነው" ሲሉ ሃብታም አገራት ላይ የታየውን የሞራል ውድቅትና ስግብግብነትን ተችተው ነበር።

በታላቋ ብሪታኒያ፣ በአሜሪካ በአውሮጳ፣ በሩሲያና በቻይና የተመረቱ ክትባቶች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው። ሆኖም ክትባቶቹ ለአገራቱ እየደረሱ ያሉበት መንገድ ኢፍትሐዊነት የሚንጸባረቅበት ነው።

ሃብታም አገራት 4 ቢሊዮን ተኩል የሚሆኑ የክትባት ብልቃጦችን ለራሳቸው ደብቀው ይዘዋል። ነገር ግን መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት 670 ሚሊዮን ጠብታዎችን ብቻ ነው ማግኘት የቻሉት።