አሜሪካ በሰባት የቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ እገዳ ጣለች

አንድ ባለሙያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በብቃታቸው የላቁ ኮምፒውተሮችን ለቻይና ጦር ሠራዊት እየገነቡ ነው ያለቻቸውን ሰባት የቻይና የቴክኖሎጂ ተቋማትን ጥቁር መዝገቧ ውስጥ እንዳስገባቻቸው አሜሪካ አስታወቀች።

ይህ እርምጃ የጆ ባይደን አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ቻይና የአሜሪካንን የረቀቁ ቴክኖሎጂዎችን እንዳታገኝ የሚያደርግ የመጀመሪያው ውሳኔ ነው ተብሏል።

በዚህም መሠረት ሦስት ኩባንያዎችና አራት የቻይና ብሔራዊ የላቁ የኮምፒዩተሮች ምርምር ማዕከል ቅርንጫፎች ናቸው ከዚህ በፊት ከነበራት ጥቁር መዝገብ ውስጥ ያካተተቻቸው።

ይህ እርምጃም የአሜሪካ ኩባንያዎች የትኛውንም አይነት ቴክኖሎጂ ለእነዚህ የቻይና ተቋማት በሚያቀርቡበት ጊዜ ከአገሪቱ መንግሥት ተገቢውን ፈቃድ እንዲያገኙ ያስገድዳል።

የአሜሪካ የንግድ መሥሪያ ቤት እንዳለው እነዚህ ተቋማት በቻይና ጦር ሠራዊት ሥር ላሉ ክፍሎች የመጠቁ ኮምፒውተሮችን (ሱፐር ኮምፒውተርስ) በመገንባት ሥራ ውስጥ የሚሳተፉና የጅምላ እልቂትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ጦር መሳሪያዎችን ለመስራት በሚካሄዱ ፕሮግራሞች ውስጥም ያሉ ናቸው።

በአሜሪካ ጥቁር መዝገብ ውስጥ እንዲገቡ የተደረጉት ድርጅቶች ቻይና እያካሄደችው ባለው የላቁ ኮምፒውተሮች ግንባታ ውስጥ ቀዳሚ ሚና ያላቸው ሲሆን በተጨማም አገሪቱ በኮምፒውተር "ቺፕ" ምርት እራሷን እንድትችል ጥረት የሚያደርጉ ናቸው ተብሏል።

የአሜሪካ የንግድ ሚኒስትር ጊና ሬይሞንዶ እንዳሉት አዲሱ የባይደን አስተዳደር "ቻይና አለመረጋጋትን ሊያስከትል በሚችል ሁኔታ ወታደራዊ ተቋሞቿን የማዘመን ሥራዋን ለመከላከል የአሜሪካንን ቴክኖሎጂ እንዳትጠቀም ታደርጋለች" ብለዋል።

የቀድሞው የትራም አስተዳደር የስልክ አምራቹን ሁዋዌን ጨምሮ የአሜሪካንን ቴክኖሎጂ ለወታደራዊ ግልጋሎት እያዋሉ ነው ብሎ የጠረጠራቸውን በደርዘኖች የሚቆጠሩ ተቋማትን ለይቶ ነበር።

በአሁኑ የጆ ባይደን ውሳኔ ጥቁር መዝገብ ውስጥ እንዲገቡ የተደረጉት የቻይና ተቋማት በኮምፒውተር ቴክኖሎጂው ዘርፍ በጣም ተፈላጊ የሆኑ የቴክኖሎጂ ግብአቶችን ከአሜሪካ ለመግዛት ሲፈልጉ ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።

ይህ እግድ በዋናነት መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉ ተቋማት ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን ጥቁሩ መዝገብ ውስጥ ለተካተቱት የቻይና ድርጅቶች እንዳይሸጡ የሚያግድ ሲሆን፤ ነገር ግን በሌላ አገር ያሉ የአሜሪካ ተቋማት ይህ ገደብ አይመለከታቸውም ተብሏል።