ነጻ ፕሬስ፡ ለሴት ጋዜጠኞች ተራራ ሆኖ የቀጠለው የኢትዮጵያ ሚዲያ

እጇ በገመድ ተተብትቦ እርሳስ ያዘ እጅ

የፎቶው ባለመብት, spukkato

የኢትዮጵያን ሚዲያ የተቀላቀለችው ከሰባት አመት በፊት ነው። መአዛ ሃደራ ትባላለች። አራት አመታትን ካሳለፈችበት የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር የተለያየችበት አጋጣሚ በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ለሴቶች ያለውን ውጣ ውረድ ያስረዳል።

የስራ መልቀቂያዋን ከማስገባቷ ከወራት በፊት ባላወቀችው ምክንያት የሴቶችን ጉዳይ የሚመለከቱ ዘገባ እንዳትሰራ መደረግ መጀመሩን ታስታውሳለች።

አዲስ የተመደበው አለቃዋ በተደጋጋሚ ሴቶችን የሚመለከት ጉዳይ ሲሆን "ስሜ ከተላከ ወዲያ በሌሎች ወንድ ዘጋቢዎች ይተካኛል" ትላለች።

በዚሁ ምክንያት አለቃዋን «ለምን» ያለችው መአዛ "ፌሚኒስት ሆነሽ ጋዜጠኛ መሆን አትችይም" የሚል ምክንያት ነበር የተሰጣት። ነገሮችን በፆታ እኩልነት አይን ማየቷ እና ሁሌም ይህንን ለመጠየቅ ወደ ኋላ አለማለቷ ለአዲሱ አለቃዋ ምቾት እንዳልሰጠው ተረድታለች።

ይህ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም የምትለው መአዛ በወቅቱ የዘጠኝ ወር ልጅ እናትም ነበረች። ልጇን ለማስከተብ በሆስፒታል ውስጥ እያለች፣ ለአለቃዋ ልጇን አስከትባ ወደ ስራ እንደምትመለስ ብትነግረውም መልሱ

"መቅረት አትችይም" የሚል ሆኖባታል።

"የሶስት አመት ፈቃድ አልወሰድኩም ነበር። በዛ ላይ በቤቱ ሕግ ልጅን ለማስከተብ ፈቃድ መጠየቅ ይቻላል" ስትል መአዛ ታስረዳለች።

ስራዋን ለመተው የመጨረሻ ምክንያት የሆነው ልጇ በመታመሟ የሁለት ቀን እረፍት መጠየቋ እና በአመታት ከምትበልጣት ባልደረባዋ እጅግ ያነሰ የደመወዝ ጭማሪ ማግኘቷ ነበር። ይህም ከብቃት ጋር የተያያዘ ያለመሆኑ አስቆጥቷታል።

የፎቶው ባለመብት, Meaza

የምስሉ መግለጫ,

መዓዛ ሃድራ

"መልኳ ላይ ማተኮር"

"ወንድ ባልደረቦቼ እኮ ሶስት ልጅ ወልደው አሁንም ይሰራሉ" ስትል መአዛ በጾታ የሚደረጉ ልዩነቶችን ታስረዳለች። ወደ ስክሪን የሚቀርቡ ሴት ጋዜጠኞች እድሜ ብሎም የሰውነት ሁኔታ እንጂ የሚያቀርቡት ይዘት ላይ ትኩረት አለመደረጉ ያበሳጫት ነበር።

"ሴት ጋዜጠኛ የፃፈችውን ዜና የሚያስተካክልላት ሳይሆን ሜካፗ እና ልብሷ ላይ ሰአታት የሚፈጅ ሰው ነው ያለው። ጠዋት ለኤዲቶሪያል ስንሰበሰብ የሴቷ አንባቢ አለባበስ እና አቀራብ ላይ እንጂ የወንዱ ሱፍ ላይ አናተኩረም" ትላለች።

መአዛ አክላም ሜካፕ መቀባት የማትፈልግ ጋዜጠኛ በቴሌቪዥን ቀርባ መታየት እንደማትችል በምሳሌነት ራሷን በማንሳት ታብራራለች። ምንም እንኳን ልምድ ቢኖራትም ሜካፕ እንዲሁም ቀሚስ ለማድረግ ባለመፈለጓ ወደ ፊት መውጣት የማይታሰብ ነበር።

"አብዛኛዋ ሴት አቅራቢ ቀረፃ አልቆ ሂውማን ሄሯን አውልቃ እስክትጥል እና ሜካፗ እስከምታስለቀቅ ነው የምትቸኩለው። ወንዶቹ ግን ለቀረፃ 10 ደቂቃ ሲቀር ነው የሚመጡት። ትኩረታቸውም የሚያቀርቡት ነገር ላይ ነው" መአዛ ታነፃፅራለች።

"የደመወዝ ጭማሪ ሲደረግ እኔ አራት አመት የምበልጣት ልጅ የተጨመረላት ጭማሪ ከኔ የአምስት ሺህ ብር ይበልጥ ነበር" ትላለች።

"ለምን ብዬ ስጠይቅ፣ 'እርሷ በቴሌቪዥን ስለምትቀርብ ያልሆነ ቦታ እንድትውል እና የማይሆን ልብስ ለብሳ እንድትታይ አንፈልገም' የሚል ምክንያት ነበር የተሰጠኝ። በስራ ልዩነት ቢሆን ደስ ነበር የሚለኝ። የሰጡኝ ምክንያት ግን በአጠቃላይ ለሁሉም ሴት አግባብ ያልሆነ ነበር" ትላለች መአዛ።

የምስሉ መግለጫ,

ፎዮ-አይ ኤም ኤስ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀን የሚታየውን የስርአተ-ፆታ ምጣኔ አመላካች በሚል ርዕስ ካስጠናው ጥናት ላይ የተወሰደ

ሴት የሚዲያ አመራሮች

ፎዮ አይኤም ኤስ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀን የሚታየውን የስርአተ-ፆታ ምጣኔ አመላካች በሚል ርዕስ አስጠንቶ ባለፈው ወር የታተመው ወረቀት ሰባት የመገናኛ ብዙሃንን መርጦ የሴት አመራሮችን ጉዳይ ፈትሿል። ይህ ጥናት የሴቶችን ተሳትፎ የኤዲቶሪያል ውሳኔ ሰጪ አመራሮች እና መደበኛ አመራሮች ሲል ለሁለት ከፍሎ ተመልክቶታል።

በጥናቱ ብዙ ሴት ሰራተኞች አሉት የተባለው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ካሉት 25 አመራሮች አንዷ ብቻ ሴት ናት። የኤዲቶሪያል ውሳኔ ከሚሰጡ ሃለፊዎች ደግሞ 40 በመቶው ሴቶች ናቸው።

በኢትዮጵያ ትልቁ ቀጣሪ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ካሉት 64 አመራሮች 13ቱ ብቻ ሴቶች ናቸው። እንዲሁም የኤዲቶሪያል ውሳኔ ሰጪነት ላይ ያሉ ሴቶች 16.6 በመቶው ብቻ ናቸው።

ይህ ጥናት እንደሚያሳያው በብሮድካስት የመገናኛ ብዙሃን ከህትመት የተሻለ በርካታ ሴት ጋዜጠኞች አሏቸው። ለዚህም የህትመት መገናኛ ብዙሃን ቁጥራቸው እየቀነሰ መምጣቱ እንዳለ ሆኖ ዘርፉ ሴት ጋዜጠኞችን ማቆየት አለመቻሉ ሌላው ነው።

አንድ የህትመት ሚዲያን በመምራት ከአራት አመት በላይ ያገለገለች እና በቅርቡ ፆታን መሰረት ባደረገ ጥቃት ምክንያት ስራዋን የለቀቀችው ፋሲካ ታደሰ መገናኛ ብዙሃን ለምን ጥቂት ሴት አመራሮች እንዳሏቸው ታስረዳለች።

ስምንት አመታት በጋዜጠኝነት ያሳለፈችው ፋሲካ ስለራሷ አጋጣሚ ከመናገሯ በፊት ሴት የሚዲያ መሪዎች ከወንዶች በተለየ በየዕለቱ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ታስረዳች። "አንድም ቀን ሴት አለቃ ትኖረኛልች ብሎ አስቦ ከማያውቅ ሰው ጋር መጋፈጥን ይጠይቃል" ትላለች።

"ብዙ ወንዶች ባደጉበት ማህበረሰብ እና ቤተሰብ የወንድ የበለይነት የተለመደ ስለሆነ የሴቶችን መሪነት አምኖ መቀበል ይከብዳቸዋል። ስራቸውን ስትተቺ ወይም ትዕዛዝ ሲሰጣቸው 'ንቃኝ ነው፤ ማን ስለሆነች ነው' ማለቱ ይቀናቸዋል" ስትል ፋሲካ ለቢቢሲ አስረድታለች።

ከወራት በፊት ከወንድ የስራ ባልደረባዋ በይፋ የተወረወሩ በቃላት ጥቃቶች ምክንያት ስራዋን ጥላ እንደወጣች ትናገራለች። ከዚህ ቀደም ብሎም ተመሳሳይ ቃላትን ቢወረውርም ስሜታዊ ሆኖ ይሆናል ብላ ማለፏን ትገልፃለች ፋሲካ።

" አለቆቼን ጨምሮ ሁሉም ባልደረቦቼ ባሉበት ጾተኝነት የተጫናቸው መልዕክቶች የሆነ መልክት ላከ። ይህንን መልክት ለወንድ ባልደረባው ቢሆን በድፍረት እንደማይልከው አውቃለሁ" ትላለች።

በጋዜጣው ከፍተኛ የሃላፊነት ደረጃ ላይ ብትገኝም " ነገሩን ያለልክ አጋነንሽው" ከመባል ባለፈ አዳማጭ ማጣቷን ትናገራች። በዚህ ምክንያት ስራዋን ለመልቀቅ መወሰኗን ብሎም ድርጊቱን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ማሰቧን አስታወቀች።

በዚህ ወቅት ነበር ድርጅቱ " የስራ ቦታን የሚመጥን ቋንቋ አልተጠቀመም፤ ከዛ ውጪ ሌላ ችግር አላየንበትም" በሚል የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የፃፈው። በቅድሚያ በዚህ ጉዳይ ላይ ምርመራ ተደርጎ መቀጣትም ካለበት መቅጣት ብሎም ይቅርታ መጠየቅ ካለበት መጠየቅ እንጂ ይህ አካሄድ ትክክል አይደለም በሚል ተሟግታለች ፋሲካ።

" ብዙ ሰው ይህ በሕግ የሚያስጠይቅ ጥፋት መሆኑን አያውቅም። የአሰሪ ሰራተኛ ሕጉ እኮ ይህንን በግልፅ ደንግጓል። ሃላፊዎች ፆታን፣ ሃይማኖትን እና ብሔርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ላይ ምላሽ ካልሰጡ በሕጉ ይጠየቃሉ። ይህንን የሚመጥን እርምጃ ያለመውሰዳቸው ከኔ ባለፈ ለሌላውም ሰው የሚያስተላልፈው መልክት ያሳስበኛል። ይህ ኒውስ ሩም ለኔ ስለማይሆን ጥዬ ወጥቻሁ" ትለላች ፋሲካ።

የፕሬስ ነፃነትን ከሴት ጋዜጠኞች መብት እና ደህንነት ጋር ምን አገናኘው?

ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው ሲፒጄ የሰሃራ በታች ተወካይ ሙቱኪ ሙሞ እንደሚሉት ሴት ሰራተኞች ብሎም ሃላፊዎች የሌሉት ተቋም የሴትን እይታ ማጣቱ ችግሩን የፕሬስ ነፃነት ችግር ያደርገዋል ሲሉ ይሞግታሉ።

በተለይም በአፍሪካ ሴት ጋዜጠኞች ከወንድ የስራ ባልደረቦቻው ጋር ተመሳሳይ ፈተናዎችን ይጋራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሴት በመሆናቸው ብቻ ተጨማሪ ፈተናዎች ይጋፈጣሉ። ይህ በሞያው ውስጥ ለመቆየት አዳጋች ያደርግባቸዋል ይላሉ።

" በዩጋንዳ የተቃዋሚ ፓርቲ የጠራውን መግለጫ ለመዘገብ የተሰበሰቡ ጋዜጠኞች ላይ የደረሰው ጥቃት ትዝ ይለኛል። ፖሊስ ወንድ ጋዜጠኞችን ሲደበድብ ሴቷም እኩል የመደብደብ እና የመታሰር አደጋ ነበር የተጋረጠባት። ነገር ግን ማሕህበረሰቡ ሴቶች ሊሰሩት ይገባል ብሎ ከሚጠብቃቸው ስራዎች ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ችግሮችን ትጋፈጣለች" ሲሉ ሙቱኪ ያስረዳሉ።

በዚሁ ክስተት ላይ የነበረች ሴት ጋዜጠኛ ባለቤቷ " ይህንን ስራ ወይም እኔን ምረጪ" እንዳላት ማንበባቸውንም ያክላሉ።

ሴት ጋዜጠኞች ከአለቆቻቸው፣ ከማህበረሰቡ፣ ከስራ ባልደረቦቻው የሚያጋጥማቸውን ችግር ሽሽት ስራቸውን ሲተዉ የሚወዱትን ስራ መስራት ባለመቻላቸው በቀዳሚነት የሚጎዱት ጋዜጠኞቹ ራሳቸው ናቸው ይላሉ።

ነገር ግን አንድ የመገናኛ ብዙሃን የሴቶችን እይታ ያጣ ስራ መስራቱ ትልቅ ጉዳት ሲሆን ማህበረሰቡም የሚያገኘው የመረጃ እይታ ብዝሃነት የሌለው መሆኑ ችግሩን ከፕሬስ ነፃነት ጋር ያያይዘዋል ይላሉ።

በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶችን ዋቢ የሚያደርጉት ተወካይዋ ሴት ጋዜጠኞች ከወንድ ጋዜጠኞች ጋር ሲነፃፀር የበለጠ ለዲጂታል ጥቃቶች ተጋላጭ መሆናቸውን ያነሳሉ።

"በእነዚህ የስነ ልቦና ጥቃቶች ምክንያት ሴት ጋዜጠኞች ራሳቸውን ሳንሱር ማድረግ ይጀምራሉ። ይህም በቀጥታ የፕሬስ ነፃነት ላይ ጫና እያሳደረ ነው ማለት ነው" በማለት ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ተቋማቸው ለጋዜጠኞች መብት የሚከራከረው ለማህበረሰቡ መብትም ጭምር እንደሆነ የሚገልፁት ሙቱኪ የመገናኛ ብዙሃን በሴት ጋዜጠኞች መመራት በተዘዋዋሪ ከፕሬስ ነፃነት ጋር ይገናኛል ይላሉ።

" አንድ ተቋም ሃብቱን የት ላይ ማፍሰስ እንዳለበት፣ ለየትኛው የምርመራ ፕሮጀክት ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት እና የፊት ገፅ ዜናው ምን ይሁን የሚለውን የሚወስኑት ሃላፊዎቹ ናቸው። ሴት ሃላፊ ከሌለው የሴቶችን እይታ ያጣ ውሳኔ ስለሚወስን ይህ የፕሬስ ነፃነት ላይ የራሱን ጫና ያመጣል" ይላሉ።

አክለውም ሴቶች አንድ አይነት አመለካከት ያላቸው ተመሳሳይ ቡድን እንደሆኑ የማሰብ ልምድ አግባብ አይደለም ሲሉም ያስረዳሉ። ይልቁንም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚም ሆኑ ማህበራዊ ዘገባዎች በአጠቃላይ የሴትን እይታን እንዲያካትቱ ማስቻል ቁልፍ ነው። ይህም ተመልካቾች ወንዶች ብቻ ባለመሆናቸው እና የማህበረሰቡንም እይታ አንድ ወጥ እንዳይሆን ያደርገዋል ብለዋል።

መፍትሄው ምንድን ነው?

ያጋጠማት ፈተና አይኗን እንደከፈተላት የምትናገረው መአዛ አሁን ላይ በራሷ የዩትዩብ ቻናል በተለያዩ ሞያ ያሉ ሴቶችን በመጋበዝ ለወጣት ሴቶች ምክር የሚሰጡበትን ፕሮግራም ታቀርባለች።

መፍትሄው የሴት ጋዜጠኞች ማህበር ባይጠናከር እንኳን እርስ በእርስ መረዳዳት መሆኑን አጽንኦት ትሰጠዋለች። ሴቶች በእጃቸው ሚዲያን ይዘው ሲጨቆኑ ዝም ማለት እንደሌለባቸውም ትገልፃለች።

ቀድመው ወደ ሞያው የገቡ ሴት ጋዜጠኞች ለአዳዲሶቹ ስራዬ ብለው የማለማመድ ስራ ይስሩ የምትለው መአዛ "ወንዶቹ እኮ ይነጋገራሉ፤ እኛም የእህትማማችነት ስሜት ካላዳበርን ነገም የሚመጡ ልጆች ከዜሮ ይጀምራሉ" ስትል ታሳስባለች።

መአዛ "ሴት ጋዜጠኛ ከሰው ከተግባባች፣ ወጥታ ከተዝናናች እና የምትፈልገውን ስታደርግ ከታየት ይቺ ከሁሉም ጋር ናት ትባላለች። ከዚህ ተቃራኒ ከሆነች ደግሞ መነኩሴ ይሏታል" የምትለው መአዛ " የኔ ምኞት ይሄ እንዲቆም ነው፤ ሴት ጋዜጠኛ ሳይሆን ጋዜጠኛ ብቻ የምትባልበት ግዜ ይናፍቀኛል። ልብሷ፣ መልኳ፣ ፀጉሯ ሳይሆን በምትሰራው ስራ የምትገመትበት ኢንዱስትሪ ሆኖ ማየት ህልሜ ነው" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

" የትም ብሄድ መፍትሄ አላገኝም። አርፌ ብቀመጥ ይሻለኛል" በሚል ችግሮቹ መድበስበሳቸው ብዙ ተቋማትም የሴት ሰራተኞቻቸውን ደህንነት በቸልታ እንዲያዩት ምክንያት መሆኑን የምታሰረዳው ደግሞ ፋሲካ ነች።

" የደረሰባቸውን ቢናገሩ ስራቸውን ስለሚያጡ በዝምታ የሚያልፉት ብዙዎች ናቸው" ትላለች።

ተቋማት የሴት ጋዜጠኞቻቸውን ደህንነት ከቁብ የማይቆጥሩበት ዋነኛው ምክንያት የሞያ ማህበራት የቅስቀሳ (አድቮኬሲ) ስራ መዳከም መሆኑንም ታብራራለች። የሴት ጋዜጠኞች ማህበርን ጨምሮ ሌሎች የሞያ ማህበራት መብት ሲጣስ አደባባይ ወጥቶ መከራከር አለመቻለቸው ለሚዲያ ሃላፊዎች ማን አለብኝነት አስተዋፅኦ አለውም ትላለች።

በተጨማሪም የፌሚኒስት ንቅናቄዎች መስራት የሚገባቸው ቦታዎች ላይ መስራት አለመቻለቸው ሌላው ክፍተት ነው። " አዲስ አበባ ውስጥ በርካታ የፌሚኒስት ንቅናቄዎች አሉ፤ አቅማቸውን የሚጨርሱት በሌላ ቦታ ነው። የስራ ላይ ደህንነት ዋነኛው አተኩረው መስራት ያለባቸው አካባቢ ነው ብዬ አምናለሁ" ትላለች።

እነዚህ ማህበራት ችግሮቹ ሳይመጡ ስልጠና መስጠት እና ተቋማት የውስጥ አሰራራቸውን እንዲፈትሹ ማድረግ ይገባል። " በአንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ፆታዊ ጥቃት እንዳለም እኮ እንሰማለን። እነዚህ ጋዜጠኞች ይህንን ብንናገር ነገ ማንም አይቀጥረንም ብለው ዝም ይላሉ" የምትለው ፋሲካ ይሄንን ችግር ለመቅረፍ ሩቅ ብንሆን እንኳን መቀነስ አለብን ትላለች።

ሙቶኪ በኩላቸው መገናኛ ብዙሃን ከውስጥ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ብቻ ሳይሆን ከውጪም የሚገጥሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ከዘገባው በፊት የሴት ጋዜጠኞቹን ደህንነት ማስቀደም አለበት ይላሉ። በመላው አለም በዚህ ላይ የሚሰሩ በርካታ ተቋማት እንዳሉ እና ሴት ጋዜጠኞች እነዚህን ተቋማት በማግኘት አገልግሎቶቹን መጠቀም ይኖርባቸዋል ይላሉ።