ኤርትራ፡ የአሰብና ምጽዋ ወደቦች ምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?

የምጽዋ ወደብ

ስድሳ ከመቶ በላይ የዓለም ነዳጅ በሚመላለስበት የንግድ መስመር ቀይ ባሕር በኤርትራ ውስጥ ከሰሜን ወደ ደቡብ 1 ሺህ ኪሎ ሜትር ይሸፍናል።

ኤርትራ ከ300 በላይ ትላልቅና አነስተኛ ደሴቶች አሏት።

በዚህ ምጽዋና አሰብ ተብለው የሚጠሩ ሁለት የወደብ ከተሞች አሉ። ወደቦቹ ከ60 ዓመታት በፊት ብዙ የወጪና የገቢ ንግድ የሚመላለስባቸው ነበሩ።

በኤርትራ ትጥቅ ትግል ወቅት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ወደቦች ጥገና ተደርጎላቸው ከ1983 እስከ 1990 ድረስ አገልግሎት ይሰጡ ነበር።

የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ግን ኢትዮጵያ የጅቡቲ ወደብን መጠቀም ጀመረች። በዚህ ምክንያት ተዳክመው የቆዩት ወደቦች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ዳግም መነቃቃት ያሳያሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።

በአሁኑ ወቅት በንግድ መርከብ የሚሰራው የኤርትራ ባሕረኞች ማኅበር አባል የሆነው ካፒቴን መሪሕ ሃብተ የኤርትራ ወደቦችን ከባሕር ትራንስፖርት፣ ከአሳ፣ ከቱሪዝምና ከማዕድን አንጻር ከፋፍሎ ማየት ይቻላል ይላል።

የአሰብና የምጽዋ ወደቦች እቃዎችን የመጫንና የማራገፍ፣ የመጋዝን እና ሌሎች አገልግሎቶች የሚሰጡ ሲሆን በአሰብ እስከ 94 በመቶ የሚገባውና የሚወጣው ንብረት የኢትዮጵያ ንግድ እንደነበረ ቺፍ ኢንጅነር ፓውሎ አንቶንዮ ይጠቅሳል።

ከ1983 እስከ 1988 ዓ.ም 3.06 ቶን የሚደርስ ጭነት በወደቦቹ እንደተጓጓዘና እስከ 802 መርከቦች ማስተናገዱንም ይናገራል።

ከ1986 እስከ 1989 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ደግሞ ወደቦቹ እስከ 1150 መርከቦች አስተናግደዋል፤ 3.287 ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ጭነትም አራግፈዋል።

በ1989 ብቻ 2695 መርከቦች ሲያስተናግዱ 3̋95 ሚሊየን ቶን እቃ እንደተጫነና እንደተራገፈ ቺፍ ኢንጅነር ፓውሎ ይናገራል።

የወደቦቹ አቅም

  • ምጽዋ 1007 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ በአንድ ጊዜ ስድስት መርከቦች ማቆም ይችላል።
  • ይህ ወደብ 204,057 ስኴር ሜትር የመጋዝን ቦታ አለው።
  • የአሰብ ወደብ 1025 ሜትር የሚዘረጋ ና 'ሀ' ቅርጽ ያለው ወደብ ሲሆን በአንድ ጊዜ ሰባት መርከቦች የማቆም አቅም አለው
  • ወደቡ 275,320 ስኴር ሜትር የመጋዝን ቦታ ያለው ሲሆን እስከ 385 ሺ 930 ቶን የመያዝ አቅም አለው

የወደቦቹ አቅም ከጎረቤት አገሮች ጋር ሲነጻጸር

የኤርትራ ወደቦች ከጂቡቲ ወደቦች ጋር ሲነጻጸሩ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ይህ አገራቱ ከሚከተሉት ፖሊሲ ጋር የሚያያዝ ሲሆን ጂቡቲ የብዙ አገሮች የወደብ ማዕከል በመሆንዋ፣ በተለይ ከ1990 በኋላ ለኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት ስትጀምር አገልግሎት የመስጠት አቅሟ በእጥፍ እንዳደገ የኤርትራ ባሕረኛ የነበረው ካፒቴን ተስፋይ ኢትባረኽ ይናገራል።

ማሪታይም ሲልክ ሮድ በመባል የሚታወቀው የቻይና ፕሮጀክት አካል የሆነው ፖርት ሱዳንም ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ እያደገ መሆኑ ይነገራል።

የኤርትራ ወደቦች በተለይ ባለፉት ዓመታት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከየመን ጋር ለምታደርገው ጦርነት ብትጠቀምበትም ምንም አይነት ማሻሻያ አለማሳየታቸው የባሕር እንቅስቃሴ የሚከታተለው አህመድ አብዱ ይገልጻል።

ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአንድ ወቅት ለአገሪቷ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ቃለ መጠይቅ "የባሕር እንቁ የሚትባለው ምጽዋ ግን አለች? የባሕር እንቁም አይደለችም፤ ምንም አይደለችም" በማለት የምጽዋ ወደብ አቅም እንደወረደ ገልጸው ነበር።

በአሁን ወቅት በስዊድን አገር በአንድ መርከብ ላይ እየሰራ የሚገኘው ኦፊሰር ቢንያም ታደሰ "የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች በድንበር ጦርነት ምክንያት በወደብ አገልግሎት ብቻ በቢሊየን ዶላር ከስረዋል" ይላል።

ኦፊሰር ቢንያም "የኤርትራ ባሕር ግን የወደብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ብቻ የሚውል አይደለም" በማለት የተለያዩ የአሳ አይነቶች፣ የባህር እንቁ፣ የጨው ማዕድንና ሌሎች የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት የሚችሉ ሃብቶች እንዳሉት ያስረዳል።

ኤርትራ ስንት መርከቦች አሏት?

በ2002 በተደረገው ጥናት መሰረት በኤርትራ 8 የሚደርሱ ትልልቅ መርከቦች ተመዝግበው ነበር።

መርከቦቹም ዮሃና፣ በይሉል፣ ሰላም፣ አንጀሎስ፣ ደንደን፣ መረብ ጋሽ፣ ሳሊናና ኤስሮምና የሚል መጠሪያ አላቸው።

መርከቦቹ በአጠቃላይ 31245 ቶን እንደሚመዘኑ የኤርትራ ባሕረኞች ይናገራሉ።

ኤስሮም ትላቋ የጭነት መርከብ ስትሆን 12333 ቶን ትመዘናለች። ዲኤምቲ የተባለው ኩባኒያም የመርከቧ ባለቤት ነው።

በይሉል የቦት መርከብ ስትሆን መረብ ጋሽ ደግሞ በከረን ሺፒን ላይን የምትተዳደረው የነዳጅ ጫኝ መርከብ ናት።

ሳሊና መርከብ የጭነት አገልግሎት የምትሰጥ በግል የምትተዳደር መርከብ ስትሆን ዛፈ ሺፒንግ ሊይን ባለቤትዋ ነው።

"ይሁን እንጂ" ይላል ኦፊሰር ቢንያም "በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ አገልግሎት የሚሰጡ በመንግሥትና በተለያዩ ማኅበራት የሚተዳደሩ መርከቦች ሙሉ ለሙሉ ቆመው፤ ሠራተኞቻቸው በስደት በተለያዩ አገራት መርከቦች እየሰሩ ይገኛሉ።"

ከዚህ ቀደም ብዙ ወደ ሆላንድ፣ ሕንድና ፓኪስታን ተልከው የሰለጠኑ በርካታ ባሕረኞች እንደነበሩ የሚገልጸው ካፒቴን ተስፋይ በበኩሉ "ከነጻነት በኋላ በርካታ ወደ ታንዛኒያ፣ ዱባይና ኤምሬትስ ተልከው ሰልጥነው ነበር" ሲል ያስታውሳል።

ሆኖም ይህ ቀጣይነት ማጣቱን የሚናገረው ካፒቴን ተስፋይ "የኤርትራ ባሕረኞች አቅም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው ያለው" ሲል ያስረዳል።

የመጀመሪያው የኤርትራ ባሕረኞች ማኅበር በ1975 በምጽዋ ተመስርቶ ነበር። ይህ በተለያዩ ምክንያቶች መቀጠል ስላልቻለ በ2015 በስደት የተቋቋመው የኤርትራ ባሕረኞች ማኅበር እስከ 1500 የሚደርሱ አባላት አሉት።