የአሜሪካ ፖሊሶች "መተንፈስ አልቻልኩም" እያለ በሚሞት ሰው ላይ ሲሳለቁ ታዩ

ዊልያም ጄኔት የተባለውን አፍነውት

የፎቶው ባለመብት, Marshall County Jail/WTVF

በአሜሪካ እስር ቤት አንድ ታራሚን ፖሊሶች መሬት ላይ አስተኝተውት "መተንፈስ መቻል የለብህም" እያለች አንደኛዋ ፖሊስ ስትሳለቅበት እንደነበር የሚያሳይ ቪዲዮ ከሰሞኑ ወጥቷል።

ይህ ቪዲዮ እንደሚያሳየው የ48 አመቱ ዊልያም ጄኔት የተባለ ታራሚ በቴኔሲ ግዛት ማርሻል ካውንቲ እስር ቤት ውስጥ ከኋላ ታስሮና ደረቱ ከመሬት ላይ ተጣብቆ ነው።

"እባካችሁ እርዱኝ" በማለትም የእስር ቤቱን ሰራተኞች ሲማፀን ይሰማል አክሎም በተቆራረጠ ድምፅ " ሊገሉኝ ነው" ይላል።

ፖሊሶቹ ከጀርባው ተጭነውት የነበረ ሲሆን መተንፈስ አልቻልኩም እያለ ሶስት ጊዜ ሲማፀንም ሊነሱለት አልቻሉም።

እንዲያውም አንደኛዋ ፖሊስ "መተንፈስ መቻል የለብህም" በማለትም አፀያፊ ስድብ ስትሰድበው ይሰማል።

ፖሊሶቹ ላይ በቀረበው ክስ መሰረት የታራሚውንም ድምፅ በማስመሰል "መተንፈስ አልቻልኩም" ብላ የምትሳለቅ ሲሆን ሌላኛው ፖሊስ ደግሞ ሲስቅ ይሰማል።

ለአምስት ደቂቃም ያህል በዚህ መልኩ በደረቱ መሬት ላይ አጣብቀውት ነበር ተብሏል።

አንደኛው ፖሊስ በበኩሉ ታፍኖ ሊሞት ይችላል እንዲተነፍስ እናድርገው ሲል ይሰማል።

ክሱ እንደሚያስረዳው ታራሚውን በጀርባው በሚገለብጡበት ወቅት ፊቱ ወይንጠጅ ቀለም የታየበት ሲሆን ሰውነቱም በድን ሆኖ ነበር።

የታራሚው አስከሬን የምርመራ ውጤት እንደሚያሳየው ግለሰቡ መጠጥና አደንዛኝ ዕፅ በመጠቀም ናውዞ መሞቱንና ከዚህም በተጨማሪ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ለማዋል የተጠቀሙበት መንገድ እንዲያፍነው ማድረጉ ለሞቱ መንስኤዎች ተብለው ተጠቅሰዋል።

በተለይም ታራሚው ከሞተ በኋላ ጥቁር አሜሪካዊውን ጆርጅ ፍⶀይድ መሬት ላይ ደፍቀውና አንገቱ ላይ ተንበርክከው መግደላቸውን ተከትሎ ውዝግብ አስነስቷል።

ይህ ታራሚ ነጭ ሲሆን ልጁም በአባቷ ሞት ፖሊስ ተጠያቂ ነው ስትል ክስ መስርታለች።

በዚህ ክስ ላይ ሰባት ፖሊሶች ኃይልን ያለ አግባብ መጠቀም በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።