የእስራኤል እና የፍልስጥኤም የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ እርዳታ ጋዛ ደረሰ

በጋዛ የፈራረሱ ቤቶች

የፎቶው ባለመብት, EPA

በእስራኤል እና በፍልስጥኤም ታጣቂዎች መካከል የተኩስ አቁም የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ከሰዓታት በኋላ የመጀመሪያዎቹ የሰብአዊ ዕርዳታ የጫኑ መኪናዎች ጋዛ ደርሰዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ሲሆን የመልሶ ግንባታው ዓመታትን ሊፈጅ ይችላል ሲሉ ባለስልጣናቱ እየገለጹ ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ መንገድ እንዲከፈትላቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡

ለ 11 ቀናት በቆየው ግጭት ከ 250 ሰዎች በላይ የተገደሉ ሲሆን አብዛኛዎቹ ከጋዛ ናቸው፡፡ እስራኤል እና ሃማስ ድል መቀዳጀታቸውን በየፊናቸው እየገለጹ ነው፡፡

የደቡባዊ እስራኤል ነዋሪዎቹ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ቢያስደስታቸውም ብዙዎች ግን ሌላ ግጭት አይቀርም የጊዜ ጉዳይ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኬሬም ሻሎም መተላለፈፊያን ከከፈተች በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጋዦችን ጨምሮ ከተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች መድሃኒት፣ ምግብ እና ነዳጅ የጫኑ መኪናዎች ጋዛ መድረስ ጀምረዋል፡፡

ሃማስ በሚቆጣጠረው ክልል ከ 100 ሺህ በላይ ሰዎች ቤታቸውን ለቀው ሲሰደዱ ወደ 800 ሺህ የሚጠጉት ሰዎች ደግሞ ውሃ እያገኙ አይደለም ሲል የተባበሩት መንግስታት የህጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ገልጿል፡፡

የፍልስጥኤም ባለሥልጣናት ከጦርነቱ ባሻገር በኮቪድ-19 ጋር ጉዳት የደረሰበትን አከባቢ እንደገና ለመገንባት በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው ጤና ተቋማት በሺዎች የሚቆጠሩ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን ማስተናገድ ሊገደዱ ስለሚችሉ የጤና ባለሙያዎች እና ቁሳቁስ ድጋፍ በአስቸኳይ እንዲደረግ የዓለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ማርጋሬት ሀሪስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጋዛ ለዓመታት በእስራኤልና በግብፅ የእንቅስቃሴ ገደብ ስትታሽ ቆይታለች ምክንያቱ ደግሞ ሁለቱም አገራት መተላለፊያ ከከፈቱ የጦር መሳሪያዎች ወደ ሃማስ ይደርሳሉ በሚል ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፍልስጥኤም ስደተኞች ጉዳይ እንዳስታወቀው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን ለመለየት እና ለመርዳት 38 ሚሊዮን ዶላር አስቸኳይ ድጋፍ ጠይቋል፡፡

የጋዛ የቤቶች ልማት ሚኒስቴር 1 ሺህ 800 መኖሪያ ቤቶች ለመኖር የማይመቹ መሆናቸውንና 1 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ መውደማቸውን አስታውቋል፡፡

ጋዛ ውስጥ በእስራኤል እና በፍልስጥኤም ታጣቂዎች መካከል ለሳምንታት የተካሄደው ውጊያ ግንቦት 10 ቀን በአል-አቅሳ መስጂድ በተነሳ ግጭት ነው የተቀሰቀሰው፡፡

ሃማስ እስራኤል ከቦታው እንድትወጣ ካስጠነቀቀች በኋላ ሮኬቶችን መተኮስ የጀመረች ሲሆን እስራኤል በበኩሏ የአየር ጥቃቶችን አስከትላለች፡፡

በጋዛ ከ 100 በላይ ሴቶችንና ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 248 ሰዎች መገደላቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ አስታውቋል፡፡ እስራኤል በውጊያው ቢያንስ 225 ታጣቂዎችን መግደሏን አስታውቃለች፡፡ ሃማስ ስለደረሰው ጉዳት አሃዝ አልገለጸም፡፡

በእስራኤል ሁለት ህፃናት እና አንድ የእስራኤል ወታደርን ጨምሮ 13 ሰዎች መገደላቸውን ተገልጿል።

ብዙ የአይሁድ ቤተሰቦች ከቦምብ መጠለያ ምሽጎች እየወጡ ሲሆን ሁሉም ትምህርት ቤቶች እሁድ ሲከፈፈቱ የተጣሉ የአስቸኳይ ጊዜ ገደቦች ተነስተዋል፡፡

የእስራኤል ጦር እንዳስታወቀው በግጭቱ ወቅት ታጣቂዎች ከ 4 ሺህ 00 በላይ ሮኬቶችን መተኮሱን ገልጾ ከእነዚህ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት በአየር መከላከያዎቻቸው አክሽፈዋል፡፡

ከመከላከያው ያለፉ ሮኬቶች መኖሪያ ቤቶችን፣ ምኩራቦችን እና ሌሎች ሕንፃዎች ጎድተዋል፡፡

ብዙዎቹ ሮኬቶች በደቡባዊ እስራኤል እንደ አሽኬሎን ባሉ ከተሞች ላይ የተተኮሱ ሲሆን የአከባቢው ነዋሪ ሆነችው ታሚ ዛሚር ግጭቱ በመቆሙ ደስተኛ እንደሆነች ገልጻ "ሌላ መባባስ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነው" ስትል ለሮይተርስ ተናግራለች፡፡

የ 25 ዓመቱ ዳን ኪሪ ሃማስ እስኪፍረከረክ ድረስ እስራኤል ጥቃት መሰንዘሯን መቀጠል እንዳለባት በመግለጽ "የጋዛ ዘመቻ በድጋሚ እስኪጀመር ድረስ የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው" ብሏል፡፡

ትላንት ከጁምአ ሰላት በኋላ በአል-አቅሳ ግቢ በተፈጠረው ግጭት የተኩስ አቁም ሙከራው ተፈትኗል ፡፡ በእስራኤል ፖሊሶች እና በፍልስጥኤም ሰልፈኞች መካከል በተፈጠረው ግጭት ቢያንስ 20 ፍልስጥኤማውያን ቆስለዋል ሲሉ የሕክምና ባለሞያዎች ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ግጭቱን ለመፍታት የሁለት መንግስታት መፍትሄ ብቸኛው መንገድ መሆኑን ገልጸው አካባቢው በማያሻማ ሁኔታ የእስራኤል የመኖር መብትን እስካልተገነዘበ ድረስ ሠላም ሊኖር እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

አሜሪካ በጋዛ ላይ የደረሰው ጉዳት ተከትሎ መልሶ ለመገንባት ዓለም አቀፍ እርዳታ እንደምታስተባብር ገልጸዋል፡፡