ሌዲ ጋጋ በደረሰባት መደፈር በማርገዟ 'አዕምሮዬ ተቃውሶ ነበር' አለች

ሌዲ ጋጋ

የፎቶው ባለመብት, Apple TV+

ስመ ጥሩዋ ሙዚቀኛ ሌዲ ጋጋ በደረሰባት መደፈር በማርገዟ ከፍተኛ የአዕምሮ መቃወስ አጋጥሟት እንደነበር ሰሞኑን ተናግራለች።

ጥቃቱ ሲደርስባት የ19 አመት ሙዚቃ ጀማሪ የነበረች መሆኗን ገልፃ የደፈራትም ግለሰብ የሙዚቃ ፕሮዲውሰር ነበር ብላለች።

ፕሮዲውሰሩ ልብስሽን ካላወለቅሽ አልበምሽን እናቃጥለዋለን ብሎም አስፈራርቷት ነበር።

በደረሰባት መደፈር አረገዘች።

በአንድ ወቅትም አርግዛ ታማ እያስመለሰች በነበረችበት ወቅት ደፍሮኛል ያለችው ግለሰብ ወደ አንድ ጥግ እንደጣላትም ተናግራለች።

በወቅቱ ለአዕምሮ መቃወስ አጋልጧትም እንደነበር የተናገረችው ሌዲ ጋጋ በተለይም ከአመታት በኋላም ተደራራቢው ስቃይ ከፍተኛ ለሆነ የአዕምሮ መቃወስና ሙሉ በሙሉ ራሷንም አጥታ እንደነበር ይፋ አድርጋለች።

በመድረክ ስሟ ሌዲ ጋጋ የምትታወቀው ስቴፋኑ ጌርማኖታ ይህንን የተናገረችው ኦፕራህ ዊንፍሬይና ልዑል ሃሪ በጥምረት በሚያቀርቡት 'ዘ ሚ ዩ ካንት ሲ' (ማየት የማትችሉት እኔን) የሚል ስያሜ የተሰጠው የአፕል ቴሌቪዥን ተከታታይ ዝግጅት ላይ ባደረገችው ቆይታ ነው።

ዝግጅቱ የአዕምሮ ጤንነት ላይ ግንዛቤን ለመፍጠር ያለመ ነው። ስለደረሰባት ጥቃት በምታወራበት ወቅት በእንባ የታጠበችው ሙዚቀኛዋ ይህ መደፈር የደረሰባትም የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን በተቀላቀለችበት ወቅት ነው።

በደረሰባት ከፍተኘ መቃወስም አንዳንድ ነገሮችን በሙሉ አላስታውስም ብላለች። የ35 አመቷ ሙዚቀኛ የደፈራትን የሙዚቃ ፕሮዲውሰር ማንነት ለመግለፅ ፈቃደኛ አይደለችም።

"ከሚ ቱ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ አንዳንዶች ጥቃት ያደረሱባቸውን ግለሰቦች ማንነነት መግለፅ እፎይታ ይሰጣቸዋል። ይሄም ይገባኛል። ነገር ግን ይህንን ግለሰብ ስሙን መስማትም ሆነ ማዬት አልፈልግም" ብላለች።

ሌዲ ጋጋ ስለ መደፈሯ መጀመሪያ ይፋ ያደረገችው በአውሮፓውያኑ 2014 ነው። ከዚህም በተጨማሪም በሙዚቃዎቿ 'ስዋይን' እና ' ቲል ኢት ሃፕንስ ቱ ዩ' ጥቃቷን አንስታ ዘፍናለች።

በተለይም አንደኛዋ ሙዚቃዋ በአሜሪካ ኮሌጅ ካምፓሶች ላይ ስለሚደርሱ ጥቃቶች የሚያሳየው 'ሃንቲንግ ግራውንድ' የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም አጃቢ ነበር። በዚህም በ2016 ለኦስካር ሽልማት ታጭታ ነበር።

ከአመታት በኋላመ የአዕምሮ መቃወስ እንዲሁ እንዳጋጠማት ተናግራ ከሁለት አመታት በፊትም 'ስታር ኢዝ ቦርን' ለሚለው ሙዚቃዋ የኦስካር ሽልማት ስትቀበል በዚሁ የአዕምሮ ጤና እክል ውስጥ ነበረች።