ኮሮናቫይረስ፡ በእርግዝና ወቅት በኮሮና መያዝኮ ህፃናት ሞተው የመወለድ አደጋን ከፍ ሊያደርግ ይችላል- ጥናት

እርጉዝ የሆነች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በመውለጃ ሰሞን በኮሮናቫይረስ መያዝ ሞተው የሚወለዱ ህፃናትን እና ያለጊዜው የመውለድ ዕድልን ከፍ ሊያደርግ ይችላል ሲል በእንግሊዝ የተካሄደ አንድ ትልቅ ጥናት ገልጿል።

ነገር ግን አጠቃላይ ቁጥሩ ሲገመገም ከፍተኛ የማይባሉ እንደሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የሳይንስ ሊቃውንት እንደሚናገሩት በእርግዝናቸው ወቅት ችግሩ የሚያጋጥማቸው ሴቶች ቁጥር ከፍተኛ ባይባልም ብቁ እስከሆኑ ድረስ ክትባት እንዲወስዱ መበረታታት አለባቸው ብለዋል፡፡

ብዙዎቹ ክትባቱ የሚሰጣቸው በዕድሜ ክልላቸው መሠረት በሚወጣው መርሃ ግብር መሠረት ነው።

ጥናቱ በአሜሪካ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ጆርናል ታትሟል፡፡

በብሔራዊ የእናቶች እና የፔርናታል ኦዲት የተመራው ምርምር እአአ ከግንቦት 2020 እና ጥር 2021 ባለው ጊዜ በእንግሊዝ ከወለዱ ከ 340 ሺህ በላይ ሴቶችን መረጃ ተመልክቷል፡፡

ሁሉም ሴቶች ለመውለድ ሲገቡ ምልክት ቢኖራቸውም ባይኖራቸውም ቫይረሱ እንዳለባቸው ለማወቅ ተመርምረዋል፡፡

በጥናቱ መሠረት

* 3 ሺህ 527 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል

* ከነዚህ ውስጥ 30 የሚሆኑት ልጆች ሞተው ነው የተወለዱት (ከ 24 ሳምንት እርግዝና በኋላ የሚከሰት ሞት ነው)

* የሳይንስ ሊቃውንት እንደሚሉት ቫይረሱ ካለባቸው 1 ሺህ ሴቶች መካከል 8.5 ያህሉ ሴቶች የወለዷቸው ልጆች ሞተው ነው የተወለዱት

* ቫይረሱ ካልተገኘባቸው ከ 1 ሺህ ሴቶች መካከል 3.4 የሚሆኑት ሴቶች የወለዷቸው ልጆች ሞተው ነው የተወለዱት

* የኮሮቫይረስ ካለባቸው ሴቶች መካከል 12 በመቶ የሚሆኑት ያለጊዜያቸው ይወልዳሉ (ከ 37 ሳምንታት በፊት)

* ይህ ቁጥር ቫይረሱ በሌለባቸው ሴቶች 5.8 በመቶ ነው

ኮሮናቫይረስ ካለባቸው ሴቶች የተወለዱ ህፃናት ቫይረሱ ባይኖርባቸውም ቀደም ብለው ስለተወለዱ እና የበለጠ ድጋፍ ስለሚያስፈልጋቸው ልዩ የአራስ ሕፃናት ከፍተኛ እንክብካቤ ይፈልጋሉ ፡፡

የጥናቱ ተባባሪ አጥኝ የሆኑት ፕሮፌሰር አስማ ካሊል ሴቶች እና የጤና እንክብካቤ ሠራተኞች ሊከሰቱ የሚችሉትን አደጋዎች መገንዘባቸው አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

አክለውም "ጥናቱ የኮቪድ -19 ባለባቸው ነፍሰ ጡር ሴቶችን የእርግዝና ውጤቶች በመግለጽ በእንግሊዝ ትልቁ ነው" ብለዋል፡፡

"ያለህይወት የሚወለዱ ልጆች እና ያለጊዜ ወሊድን መጠኑ ዝቅተኛ ቢሆንም ጥናቱ ሴቶች ላይ ሞተው የሚወለዱ ህፃናትን ወይም ያለጊዜው የመውለድ አደጋ ሊጨምር እንደሚችል ያሳያል" ብለዋል፡፡

"ይህ የኮቪድ -19 ክትባት ለነፍሰ ጡር ሴቶች አስፈላጊ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ይህም ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን የአራስ ሕፃናቱንም አደጋን ይቀንሰዋል፡፡"

ከሮያል ሚድዋይፈርስ ኮሌጅ ባልደረባዋ ዶ/ር ሜሪ ሮስ ዴቪይ በበኩላቸው ክትባቱ ሰዎችን ከቫይረሱ ለመጠበቅ ቁልፍ መሆኑን ተስማምተዋል፡፡

አክለውም "ችግሩ አነስተኛ ቢሆንም አስፈላጊው መልዕክት ነፍሰ ጡር ሴቶች እንደ ሁላችንም በቫይረሱ የመያዝ ዕድልን ለመቀነስ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መቀጠል እንዳለባቸው ነው።"

"ይህም አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እጅን መታጠብ እና የአፍና አፍንጫ ጭንብል ማድረግን ያጠቃልላል" ብለዋል፡፡