የፍቅር ጓደኛ መፈለጊያው ቲንደር ትንኮሳዎችን ለመከላከል መንገድ ቀይሻለሁ አለ

የቲንደር አርማ

በበይነ-መረብ የፍቅር ጓደኛን ለመፈለግ የሚያግዘው ቲንደር የተሰኘው መተግበሪያ የቃላት ትንኮሳዎችን ለመከላከል የጸያፍ መልዕክቶችን በመመርመር ሃሳቡን ለማስቀረት ጸሐፊውን መልዕክቱን ከመላኩ በፊት ቆም ብሎ እንዲያስብ ይጠይቃል፡፡

ለዚህም በተጠቃሚዎች ከሚደርሱት መልዕክቶች "ጎጂ ቃላትን" የሚለይ ያለሰው ጣልቃ ገብነት የሚሠራ ቴክኖሎጂ ይጠቀማል፡፡

ቲንደር "እርግጠኛ ነዎት?" በሚል የጠራው ሲስተም በሙከራዎች ወቅት 10 በመቶ ያህል "የተላኩ መልእክቶች ላይ የተጻፉ ተገቢ ያልሆነ ቃላትን ቀንሷል" ብሏል፡፡

ኢንስታግራም እና ትዊተር ጸያፍ አስተያየቶችን እና ትዊቶችን ለመለየት ቀደም ሲል ጀምረው ተመሳሳይ ስርዓቶችን ሲጠቀሙ ቆይተዋል ፡፡

ኢንስታግራም ተጠቃሚዎችን "በእርግጠኝነት ይህንን መለጠፍ ይፈልጋሉ?" ሲል በፎቶ ስር የሚሰጡ አስተያየቶች ውስጥ ጸያፍ ወይም የትንኮሳ ቃላትን ከለየ ይጠይቃል።

ትዊተር ደግሞ በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ሰዎች "ጎጂ ወይም አፀያፊ" ቋንቋ የያዙ መልዕክቶችን ከመለጠፋቸው በፊት ትዊቶቻቸውን እንዲገመግሙ መጠየቅ እንደሚጀምር አስታውቆ ነበር፡፡

ቲንደር የጸያፍ ሐረግ ያለበትን መልዕክቶችን ለሚቀበሉ ሰዎች 'ይህ ይረብሽዎት ይሆን?' ሲል ቀደም ሲል ጀምሮ ይጠይቃል።

አዲሱ ስርዓት ግን መልዕክቱ ከመላኩ በፊት ጸሐፊው እንደገና እንዲያጤን ይጠይቃል፡፡

የፍቅር ጓደኛ መፈለጊያ መተግበሪያው በሙከራው ወቅት ማስጠንቀቂያውን የተመለከቱ ሰዎች "ለሚቀጥለው ወር ተገቢ ላልሆኑ መልእክቶቻቸው የመጠየቅ ዕድላቸው አነስተኛ ነው" ብሏል፡፡