ቅሬታ ያቀረቡ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲ ዳግም ምደባ ሰኞ ይፋ ይሆናል ተባለ

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አርማ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Science and Higher Education - Ethiopi

በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ወስደው በተመደቡበት ዩኒቨርስቲ ቅሬታቸውን ያቀረቡ ተማሪዎች ዳግም ምደባቸውን ከመጪው ሰኞ ግንቦት 16፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ በበይነ መረብ ማየት እንደሚችሉ ተገልጿል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገፁ ባወጣው መግለጫ 23 ሺህ 71 ቅሬታዎች በአካልና በቅሬታ ማቅረቢያ ድረገፁ ቀርበውለት ነበር።

ከነዚህም ቅሬታዎች መካከል 386 ተማሪዎች በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ተምረው በማህበራዊ ሳይንስ፤ ወይም በማህበራዊ ሳይንስ ተምረው በተፈጥሮ ሳይንስ የተመደቢ ሲሆኑ ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው ይህም ሙሉ በሙሉም ተስተካክሏል ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ የጤና ችግር ኖሯቸው ማስረጃ ያቀረቡ፣ ነፍሰ ጡሮችና ከሁለት አመት በታች ያሏቸው ህፃናት ሴቶች፣ ተመሳሳይ ፆታ ያላቸው መንትዮች በስህተት የፆታ ስህተት የተመዘገቡ ተማሪዎች ሁኔታዎችን አጣርቷል።

ሚኒስቴሩ በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው አይነ ስውራን፣ መስማት የተሳናቸው እና አካል ጉዳተኞች አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደሮች ጉዳይንም በልዩ ሁኔታ መታየቱን ጠቁሟል።

እነዚህንም ማጣራት ካደረገ በኋላ ከቀረቡት ቅሬታዎች መካከል 1 ሺህ 891ዎቹ ምላሽ ማግኘታቸውን አስታውቋል።

የተመደቡበት ተቋም ከመኖሪያ አካባቢያቸው ርቀት አለው ብለው ቅሬታ ያቀረቡ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ በህክምና ማስረጃ ያላቀረቡ እና የሃሰተኛ ማስረጃ ያቀረቡም ተጣርተው ከዚህ ቀደም በተመደቡበት እንዲመደቡ መደረጉም ሰፍሯል።

ሚኒስቴሩ ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትርን ዋቢ አድርጎ እንዳለው ዩኒቨርስቲዎች አዲስ ገቢ ተማሪዎችን እስከ ግንቦት 30፣ 2013 ዓ.ም ቅበላ እንደሚያደርጉ ነው። በተዘረጋው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሰኔ 1፣ 2013 ዓ.ም ትምህርት ይጀመራል።

በ2012 ዓ.ም ከፍተኛ ውጤት ካስመገቡት መካከል 206 ሴትና ወንድ ተማሪዎች የማበረታቻ ስርአት እንደተዘረጋም ተገልጿል።

ለተማሪዎቹ ማበረታቸው እንዲሆኑ ተብለው ከተጠቀሱ ጉዳዮች መካከል በአንደኛ ደረጃ በመረጡበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋምና የትምህርት ዘርፍ እንዲመደቡ፣ ተጨማሪ የትምህት እድል እንዲመቻችላቸውም እንደሚሰራም ሚኒስትሩ መናገራቸው ተጠቁሟል።

በዚሁ አመት የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ከተፈተኑ 343 ሺህ 832 ተማሪዎች መካከከል 147 ሺህ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ተቋም የሚያስገባቸውን ውጤት አምጥተዋል።