ኤል ሳልቫዶር፡ በቀድሞ የፖሊስ መኮንን ግቢ ውስጥ የተቀበሩ አፅሞች ተገኙ

አፅሞ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በኤል ሳልቫዶር የቀድሞ የፖሊስ መኮንን ቤት ቢያንስ የስምንት ሰዎች አጽም መገኘቱንን ባለስልጣናት ገለጹ፡፡

በግለሰቡ አትክልት ስፍራ ውስጥ በጅምላ ተቀብረው እንደተገኙም ተዘግቧል።

መቃብሩ በርካታ አጽሞች ሊኖራቸው ይችላል የተባለ ሲሆን አብዛኛዎቹ ሴቶች ወይም ሴት ልጆች እንደሆኑ ተገምቷል፡፡

ሁሉንም አጽሞች ለማውጣት ተጨማሪ ወር ሊወስድ ይችላል ተብሏል፡፡ ፖሊስ አጽሞቹ ከአስር ዓመታት በላይ ሲካሄድ የቆየ ምስጢራዊ ግድያ መኖሩን ያሳያል ብሏል፡፡

ኤል ሳልቫዶር በላቲን አሜሪካ በጾታቸው ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ከሚገደሉባት ሃገራት መካከል አንዷ ነች፡፡

የ 51 ዓመቱ ሁጎ ኤርኔስቶ ኦሶሪዮ ቻቬዝ የ57 አዛውንት እና የ 26 ዓመት ሴት በመግሉ በቻልቹዋፓ ከተማ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ቀደም ሲል በወሲብ ወንጀል ተጠርጣሪ የነበረው የቀድሞው ፖሊስ ጥንድቹን መግደሉን አምኗል፡፡

የአስከሬን ምርመራ ባለሙያዎች ከዋና ከተማዋ ሳን ሳልቫዶር በስተሰሜን 78 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘውን ቤቱን ሲፈተሹ አጽሞችን የያዙ ቢያንስ ሰባት ጉድጓዶች አግኝተዋል። አንዳንዶቹ አጽሞች ከሁለት ዓመት ያህል በፊት የተቀበሩ ናቸው ተብሏል፡፡

ባለሥልጣናት እንዳሉት ጉዳዩ ለአስርት ዓመታት ያህል የቆየ የግድያ ሰንሰለት መኖሩን ይጠቁማል ፡፡

ዓቃቤ ሕጉ ማክስ ሙኖዝ ከአንደኛው መቃብር ስምንት አጽም መገኘታቸውን ዓርብ ዕለት ገልጸዋል፡፡ የተጎጂዎችን ማንነት ለመለየት የዲኤንኤ (ዘረ መል) ምርመራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል፡፡

ባለሥልጣናት ቀደም ሲል ቢያንስ የ 24 ሰዎች አጽም ተገኝቷል ብለው ነበር፤ የተገኘው አጽም ብዛት ላይ ምንም ማብራሪያ አልተሰጠም፡፡

የኤል ሳልቫዶር ብሔራዊ ፖሊስ ዳይሬክተር ሞሪሺዮ አሪያዛ ቺካስን ጠቅሶ የቀድሞ ፖሊሶችን፣ የቀድሞ ወታደሮችንና ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ጨምሮ ቢያንስ 10 ሰዎች ክስ እየተመሰረተባቸው መሆኑን ላ ፕሬንሳ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡

ኦሶሪዮ ቻቬዝ ለአስርት ዓመታት ሰዎችን እየገደለ ቆይቷል ሊሆን ይችላል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

"ተጎጂዎችን በማህበራዊ ድር አምባ መተዋወቁንና አሜሪካ እንደሚልካቸው በማጓጓት እንዳገኛቸው ነግሮናል" ሲሉ አርሪያዛ ቺካስ ለአሶሺዬትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ገልጸዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ተጎጂዎቹ እስከ ሁለት ዓመት ዕድሜ ያሉ ሴት ልጆችን ሊያካትት እንደሚችል ኤፒ ዘግቧል፡፡ ተጠርጣሪውም ሆነ ጠበቃው አስተያየት አልሰጡም፡፡

ሐሙስ ዕለት ነጭ ልብስ የለበሱ የፎረንሲክ ሠራተኞች አፅም ከመቃብሮቹ ውስጥ ሲያስወጡ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች የጠፉ ዘመዶቻቸው ሊሆኑ ይችላሉ በሚል እምነት ከቤቱ ውጭ ተሰብስበው ታይተዋል፡፡

ኤል ሳልቫዶር ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በ 70 ሴቶች ላይ ግድያ መዝግባለች። እአአ በ 2019 ይህ ቁጥር 111 እንደነበር የፖሊስ መረጃዎች አሳይተዋል።