በቻይና ከባድ የአየር ጠባይ የ21 አገር አቋራጭ ሯጮችን ሕይወት ቀጠፈ

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በሥራ ላይ

የፎቶው ባለመብት, STR/AFP VIA GETTY IMAGES

በሰሜን ምዕራብ ቻይና በተካሄደ አገር አቋራጭ የተራራ ላይ ውድድር በተፈጠረ ከባድ የአየር ጠባይ ሳቢያ ቢያንስ 21 ሯጮች መሞታቸው ተሰማ።

ቅዳሜ ዕለት በጋንሱ ግዛት በሚገኘውና የጎብኝዎች መዳረሻ በሆነው 'የሎው ሪቨር ስቶን ፎረስት' ከፍተኛ ንፋስና ከባድ ዝናብ ተከስቶ በ100 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር የተሳተፉ ሯጮችን ክፉኛ እንደመታቸው የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

ዥንዋ የዜና ወኪል እንደዘገበው 172 የሆኑ ሯጮች መጥፋታቸውን ተከትሎም ውድድሩ ተቋርጧል።

በአደጋው ሕይወታቸው ያለፉ ሯጮች አስክሬን በነፍስ አድን ሠራተኞች ፍለጋ እሁድ ዕለት ሊገኝ ችሏል።

እንደ ዥንዋ ከሆነ ሌሊቱን በተራራማው አካባቢ የነበረው ቅዝቃዜ ፍላጋውን አስቸጋሪ አድርጎታል።

ሯጮቹን ለመታደግ በሥፍራው ከ1 ሺህ 200 በላይ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ተሰማርተዋል።

ባለሥልጣናት እንደሚሉት 151 ሯጮች በሕይወት መኖራቸው የተረጋጋጠ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል ግን ስምንቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ይህ ተራራማ ሥፍራ የሚገኝበት የባይን ከተማ ከንቲባ ዣንግ ዡችን የአደጋውን ሁኔታ ለማጣራት ልዩ የምርመራ ቡድን መዋቀሩን ተናግረዋል።

'የሎው ሪቨር ስቶን ፎረስት' 50 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት የሚሸፍን ቦታ ሲሆን አስደናቂ የድንጋይ ሰንሰለታማ ተራራዎች የተላበሰ ነው።