ልዕልት ላቲፋ፡ በቁም እስር ላይ የነበረችው የዱባዩ ገዥ ሴት ልጅ የልዕልት ላቲፋ ፎቶ መታየቱ እያነጋገረ ነው

ልዕልት ላቲፋ ከጓደኞቿ ጋር ሆና ያሳያል የተባለው ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, INSTAGRAM

የምስሉ መግለጫ,

በዚህ ፎቶ መሃል ላይ ያለችው ለወራት ያልታየችውና ድምጿ ያልተሰማው የዱባዩ ገዥ ልጅ ልዕልት ላቲፋ እንደሆነች ተነግሯል፤ ቢቢሲ የልዕልቲቱን ፎቶ ሐቀኝነት ማረጋገጥ አልቻለም

በዚህ ባገባደድነው ሳምንት የዱባይ ንጉሣዊ ቤተሰብ አባል የሆነችው ልዕልት ላቲፋ ፎቶ በኢንስታግራም በመታየቱ መነጋገርያ ሆናለች፡፡

ልዕልት ላቲፋ የዱባይ ገዥ ሴት ልጅ ስትሆን ያለችበት ሁኔታ ለረዥም ጊዜ ሲያነጋግር ነበር፡፡

ባለፈው የካቲት ቢቢሲ በምስጢር አግኝቶ ባሰራጨው አንድ ቪዲዮ ልዕልቲቱ እገታ ላይ እንዳለችና ለሕይወቷ ጭምር እንደምትሰጋ ለዓለም ይፋ አድርጋ ነበር፡፡

ከዚያ በኋላ ልዕልቲቱ ያለችበት ሁኔታ እንዲገለጽ በዱባይ ንጉሣዊያን ቤተሰቦች ላይ ጫናው በርትቶ ነበር፡፡

ቢቢሲ አሁን ይፋ የተደረገውን የልዕልቲቱን ፎቶ ሐቀኝነት ማረጋገጥ አልቻለም፡፡ ስለፎቶው ተጨማሪ ማብራሪያም ለማግኘትም ያደረገው ጥረት አልሰመረም፡፡

ሆኖም ግን የልዕልት ላቲፋ የቅርብ ጓደኛ በዚህ ፎቶ ላይ የምትታየው በእርግጥም በቁም እስር ላይ የነበረችው ልዕልት ላቲፋ ስለመሆኗ መስክራለች፡፡

ቢቢሲ የዚህ ፎቶ አወጣጥ እንዲያው በአጋጣሚ ወይም በድንገት እንዳልሆነ ይጠረጥራል፡፡

ልዕልት ላቲፋን ነጻ ለማውጣት የተመሠረተው ዘመቻ መሥራች ዴቪድ ሄይ እንዳለው በዚህ ወቅት ፎቶው መውጣቱ ምናልባት ዓለም ባሳደረው ጫና የተነሳ ለውጦች እንዳሉ የሚመሰክር ነው፡፡ ሆኖም ተጨማሪ መግለጫ ለመስጠት ጊዜው ገና ነው ብሏል፡፡

ቢቢሲ በሎንዶን የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ኤምባሲ በፎቶው ዙርያ ምላሽ እንዲሰጥ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ቢሆን በፎቶው ዙርያ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡

ሆኖም የልዕልቲቱን በመልካም ጤንነት መገኘት የሚያረጋግጥ የደረጀ መረጃን ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እንዲቀርብለት ጠይቆ ይህንኑ እየጠበቀ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡

በፎቶው ላይ ልዕልቲቱ በዱባይ የገበያ ማዕከል (ሞል ኦፍ ዘ ኢምሬትስ) ከሁለት ሴቶች ጋር ተቀምጣ የሚያሳይ ነው፡፡

የልዕልቲቱ የቀድሞ ጓደኞች እንደሚሉት ሁለቱ አብረዋት የሚታዩት ሴቶች የላቲፋ የቅርብ ወዳጆች እንደሆኑ የሚታወቁ ናቸው፡፡

ፎቶው በኢኒስታግራም ይለጠፍ እንጂ ፎቶው የተነሳበትን መሣሪያ፣ ጊዜና ቦታ የሚገልጸው የመረጃ ቋት (ሜታ ዳታ) ከፎቶው ተገድፏል፡፡

ፎቶው በኢንስታግራም የተጫነው ባሳለፍነው ሐሙስ በልዕልቲቱ ጓደኛ አካውንት ነው፡፡

ከፎቶው ሥር ‹‹ድንቅ ምሽት ከወዳጆች ጋር በዱባይ ሞል›› የሚል ተጽፎበታል፡፡

በፎቶው ላይ ከልዕልቲቱ ጋር የሚታዩት ሁለቱ ሴቶችን ቢቢሲ ለማነጋገር ሞክሮ ምላሽ አላገኘም፡፡

የሒውማን ራይትስ ባልደረባ ኬኔት ሮዝ እንደሚሉት ‹‹ፎቶው ሐቀኛ ነው ተብሎ ከታሰበ ምናልባት ልዕልቲቱ ስላለችበት ሕይወት አንድ የሚለው ነገር አለ፡፡ ቢያንስ በሕይወት ስለመኖሯ፡፡››

ቅዳሜ ይኸው ሐሙስ የተለጠፈው የልዕልቲቱ ፎቶ በድጋሚ በኢንስታግራም ታይቷል፡፡

ከቅዳሜው ምሥል ሥር ‹‹በቢቼ ማሬ ሬስቶራንት ድንቅ ምግብ ከላቲፋ ጋር›› የሚል ተጽፎበታል፡፡

ቢቼማሬ በቡርጅ ኸሊፋ የሚገኝ ቅንጡ ሬስቶራንት ነው፡፡

በየካቲት አጋማሽ የልዕልቲቱን ሁኔታ ይፋ እንዲያደርግ ጫና የበረታበት የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ላቲፋ በመልካም ጤንነት ላይ በቤተሰብ እንክብካቤ እየተደረገላት ትገኛለች ብሎ ነበር፡፡ ጊዜው ሲደርስም ከሕዝብ ጋር እንደምትቀላቀል ቃል ገብቶ ነበር፡፡

ላቲፋ የዱባዩ ገዥ ቢሊየነሩ ሼክ መሐመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም 25 ልጆች አንዷ ናት፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ከዱባይ ሸሽታ ለማምለጥ ያደረገችው ሙከራ አልተሳካላትም፡፡

ሽሽቱን ከመጀመሯ ከጥቂት ቀናት በፊት ቀርጻ ባስቀመጠችው የቪዲዮ መልዕክት ሕይወቷ መፈናፈኛ እንዳጣና ለመማርም፣ ለመጓዝም እንዳትችል እንደተደረገ ገልጻ በቁም እስር ላይ እንደሆነች ይፋ አድርጋ ነበር፡፡

ሆኖም ሽሽቱ ተደርሶበት ሳይሳካላት ቀርቷል፡፡

ለ8 ቀናት በባሕር ጉዞ ሕንድ ውቅያኖስን በማቋረጥ ላይ ሳለች በልዩ ኮማንዶዎች በቁጥጥር ሥር ውላ ወደ ዱባይ ታፍና ተመልሳ ተወስዳለች፡፡

ወደ ዱባይ ከተመለሰች ወዲህ የግዞት ኑሮ እየኖረች እንደሆነ ቢቢሲ ልዕልቲቱ በምስጢር ከቀረጸችው ቪዲዮና ከጓደኞቿ ለመረዳት ችሎ ነበር፡፡

ልዕልቲቱ የሕክምናም ሆነ የሕግ ድጋፍ እያገኘች እንዳልሆና በአንድ ቪላ ውስጥ በፖሊስ እየተጠበቀች እንደምትኖር ሾልኮ በወጣ ቪዲዮው አጋልጣ ነበር፡፡

ይህን ቪዲዮ የቀረጸችው በመታጠቢያ ቤት ውስጥ ሆና ሳለ ሲሆን ይህም የሆነው ከውስጥ መቆለፍ የምትችለው ክፍል መታጠቢያ ቤቱን ብቻ ስለሆነ እንደነበረም ተዘግቦ ነበር፡፡