በዴሞክራቲክ ኮንጎ በፈነዳ እሳተ ገሞራ በርካቶች አካባቢያቸውን ለቀው እየወጡ ነው

የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ከፍተኛ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ መከሰቱን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እየወጡ ነው።

የአገሪቷ መንግሥትም በአገሪቷ ምሥራቃዊ ክፍል የምትገኘውን ጎማ ከተማ ነዋሪዎች ማስወጣት ጀምሯል።

በንይራጎንጎ ተራራ ላይ በቀለጠ አለት ሳቢያ የተፈጠረው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የጉማ ሰማይን ጥቅጥቅ ባለ ብርቱካናማ ደመና ሸፍኖታል።

በጉማ ከተማ ሁለት ሚሊየን ሕዝብ እንደሚኖር ይገመታል።

ፍንዳታው የተከሰተውም ከዚች ከተማ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው።

በአካባቢው ለመጨረሻ ጊዜ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ያጋጠመው እአአ በ2002 ነበር።

በወቅቱ አደጋው 250 ሰዎችን የገደለ ሲሆን 120 ሺህ ሰዎችን ደግሞ ቤት አልባ አድርጓል።

ይህ አደጋ ከ19 ዓመታት በኋላ በድጋሜ ተከስቷል። ከዚህ አደጋ ለማምለጥም ነዋሪዎች እግሬ አውጭኝ እያሉ ነው።

በርካቶችም ፍራሾችንና አንዳንድ ቁሳቁሶችን ተሸክመው ወደ ሩዋንዳ ድንበር እየተመሙ ነው።

ነዋሪዎቹ ሽሽት የጀመሩት መንግሥት ካወጣው ማሳሰቢያ ቀድመው ነው።

መንግሥት ማሳሰቢያውን ያወጣው ፍንዳታው ካጋጠመ ከበርካታ ሰዓታት በኋላ ነበር።

የሩዋንዳ ባለሥልጣናት 3 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከጎማ ከተማ ድንበር አቋርጠው ሩዋንዳ እንደገቡ ተናግረዋል።

የአገሪቷ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተፈናቃዮቹ በትምህርት ቤቶችና በእምነት ተቋማት እንደተጠለሉ ዘግቧል።

ሌሎች ነዋሪዎች ደግሞ በከተማዋ ምዕራብ አቅጣጫ ወደሚገኝ ከፍታ ቦታ ሸሽተዋል።

ዛቻሬ ፓሉኩ የተባሉ ነዋሪ " አዕምሯችን ተቃውሷል፤ ሁሉም ፈርቷል። ሰዎች እግሬ አውጭኝ እያሉ ነው። ምን ማድረግ እንዳለብን አናውቅም" ሲሉ ለአሶሼትድ ፕረስ ተናግረዋል።

የእሳተ ገሞራውን ፍንዳታ ያስከተለው የመሬት ስንጥቅ የቀለጠውን አለት ወደ ጎማ ከተማ ደቡባዊ አካባቢ እንዲጎርፍ እና በአየር ማረፊያውም እንዲደርስ አድርጓል።

በበርካታ አካባቢም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጧል። የጎማ ከተማን ከቤኒ ጋር የሚያገናኘው ፈጣን መንገድም በቀለጠው አለት ተሸፍኗል።

የድኝ [ ሰልፈር] ሽታ እንደሚሸትና በርቀት የእሳት ነበልባል ከተራራው ሲፈልቅ እንደሚታይ ካሪን ምባላ የተባሉ ነዋሪ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

የእሳተ ገሞራ ፍንዳታው በተከሰተበት ቪሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ ባለሥልጣን ፍንዳታው እአአ በ2002 ካጋጠመው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ በመግለጽ በአየር ማረፊያው አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በአፋጣኝ እንዲወጡ አሳስበዋል።

የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር በኪንሻሳ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራታቸውን ተከትሎም የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ፓትሪክ ሙያይ በትዊተር ገጻቸው ላይ መንግሥት መውሰድ ስለሚገባው አፋጣኝ እርምጃዎች እየተነጋገረ እንደሆነ ገልጸው ነበር።

ነዋሪዎች ተረጋግተው እንዲቆዩ የተነገራቸው ቢሆንም አንዳንዶች የመረጃ እጥረት እንደነበር ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

በአገሪቷ ያለው የተባበሩት መንግሥታት ሠላም አስከባሪ -ሞኑስኮ በከተማ ላይ ወታደራዊ መረጃዎችን ለማግኘት የስለላ በረራዎችን እንዳደረገም ገልጾ ነበር።

የንይራጎንጎ ተራራ በዓለም ንቁ እሳተ ገሞራዎች ካሉባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። ይሁን እንጅ የዓለም ባንክ በሙስና ሳቢያ የሚያደርገውን ድጋፍ በማቋረጡ በጎማ ቮልካኖ ኦብሰርቫቶሪ [ የእሳተ ገሞራውን ሁኔታ የሚከታተል ተቋም] በቂ ክትትል እየተደረገበት እንዳልነበር ተነግሯል።

ከ10 ቀናት ገደማ በፊት ግን ይህንን የሚከታተለው አካል በተራራው ላይ ያለው እንቅስቃሴ [መንቀጥቀጥ] እየጨመረ እንደሆነ አስጠንቅቆ ነበር።

ባለፈው ዓመት የጎማ ቮልካኖ ኦብሰርቫቶሪ ዳሬክተር ካቾ ካሩሜ ለቢቢሲ የእሳተ ገሞራው የቀለጠ አለት በፍጥነት እየሞላ እንደሆነና ይህም በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ፍንዳታ የመከሰት እድሉን እንደሚጨምረው ተናግረው ነበር።

ይሁን እንጅ የመሬት መንቀጥቀጥ ከተባለው ጊዜ ቀድሞ ፍንዳታውን እንዲከሰት ሊያደርግ እንደሚችል ዳሬክተሩ ጠቁመዋል።

በርካታ ሰዎች የሞቱበት እሳተ ገሞራ የተከሰተው እአአ በ1977 ሲሆን በአደጋው ከ600 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።