ምርጫ 2013፡ በምዕራብ ሸዋ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ የድምጽ አሰጣጥ ተቋርጦ እንደነበር ተገለጸ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ ከአምቦ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ ሰኞ ማለዳ ታጣቂዎች በፈጸመወው ጥቃት ሦስት ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ኃላፊዎች ለቢቢሲ ገለጹ።
በምዕራብ ሸዋ ዞን ሊበን ጃዊ ወረዳ ኖኖ ምርጫ ክልል ሥራ በሚገኙ ሁለት የምርጫ ጣቢዎች አቅራቢያ በተፈጸመው ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ተቋርጦ እንደነበረ የአካባቢው የምርጫ አስፈጻሚ ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ በፈጸሙት ጥቃት የተገደሉት ሰዎች አንድ የአካባቢው ሚሊሻ፣ የአንድ የኦሮሚያ ፖሊስ አባል እና አንድ የአካባቢው ባለሥልጣን መሆናቸውን ተገልጿል።
ትናንት ምሽት የምርጫውን አፈጻጸም አስመልከቶ አዲስ አበባ ውስጥ ለጋዜጠኞች የተናገሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በአካባቢው መጠነኛ ችግር ተከስቶ እንደነበር ጠቁመው ነበር።
"በምዕራብ ሸዋ ኖኖ ምርጫ ክልል ሁለት ጣቢያዎች ላይ የታጠቁ ሰዎች ሂደቱን ረብሸው የድምጽ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ተቋርጦ ነበረ" ብለዋል።
ሰብሳቢዋ አክለውም "ከዚህ ውጪ ይህ ነው የሚባል የጸጥታ ችግር የለም" ብለዋል።
በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን የተለያዩ ጥቃቶችን እንደሚፈጽም የሚታወቅ ሲሆን የክልሉና የፌደራል መንግሥቱ የጸጥታ ኃይሎች ታጣቂውን ቡድን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ነው።
ትናንት ሰኞ ዕለት ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የሚያስተዳድሩት ክልል ሰላማዊ መሆኑን ጠቅሰው ባለፉት ወራት ወደ ተለያዩ የክልሉ ከተሞች መጓዛቸውን ገልጸዋል።
"ኦሮሚያ ሰላማዊ ናት። የደኅንነት ስጋት ያለው በፌስቡክና በመገናኛ ብዙሃን ላይ ነው። ዛሬ ዜጎች በሰላም እየመረጡ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ጥቃቱ የተፈጸመበት አካባቢ የምርጫ ቦርድ ኃላፊ ለቢቢሲ እንዳብራሩት ታጣቂዎቹ በከፈቱት ተኩስ ሦስት ሰዎች ተገድለው ድምጽ አሰጣጡ ተቋርጦ እንደነበር አረጋግጠዋል።
ቢቢሲ ከአካባቢ ነዋሪዎች ያገኘው መረጃው እንዳመላከተው በሊበን ጃዊ ወረዳ አገል ጎቦ ተብሎ በሚጠራው መንደር ውስጥ ሰኞ ጠዋት ከሦስት ሰዓት በኋላ ነው ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ፈጽመው ሰዎች የገደሉት።
በአካባቢው ባሉ "ሁለት የምርጫ ጣቢዎች መካከል ነው ችግሩ የተከሰተው" ያሉት የአካባቢው የምርጫ ኃላፊ፤ ሁለቱ የምርጫ ጣቢያዎች ኑኑ ባሳሌ እና አጋል ጎቦ እንደሚባሉም ተናግረዋል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዲሪርሳ ዋቁማ በታጣቂዎች ጥቃቱ መፈጸሙን አረጋግጠው፤ "ታጣቂዎች ከእሁድ ምሽት ጀምረው ምርጫው መከናወን የለበትም በማለት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር" ብለዋል።
ጨምረውም "በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ካለፈ ሰዎች መካከል አንዱ የሚሊሻ አባል ሲሆን ሌላኛቸው ደግሞ ለሥራ የተመደበ የአካባቢው ባለስልጣን ነው" ብለዋል አስተዳዳሪው።
ባለፈው ሳምንት በዚሁ በምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ ሜታ ወልቂጤ ተብላ በምትጠራ ወረዳ ውስጥ የሸኔ ታጣቂዎች ፈጸሙት በተባለው ጥቃት ቢያንስ 9 በአካባቢው በመንገድ ግንባታ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
ይህ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተለይቶ የወጣውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተሰየመ ሲሆን፤ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከሚፈጸሙ ግድያዎችና ጥቃቶች ጋር ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል።
