በኮሮና የተያዘው ኢንዶኔዥያዊ ባለቤቱን መስሎ በአውሮፕላን ሲጓዝ ተያዘ

ከኢንዶኔዥያ የሚበር አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኢንዶኔዥያ በሃገር ውስጥ በረራ ላይ በኮቪድ-19 የተያዘ አንድ ግለሰብ ሚስቱን ተመስሎ ሲበር መያዙ ተገልጿል።

ዲ ደብልዩ የተባለው ይህ ግለሰብ በአውሮፕላን ውስጥ ለመሳፈር ኒቃብ በመባል የሚታወቀውን ሙሉ የፊት መሸፈኛ ለብሶ ነበር ተብሏል።

ግለሰቡ የባለቤቱን ፓስፖርት እና ኔጋቲቭ የኮቪድ ውጤቷንም ይዞ ነበር።

በበረራው መካከል ወደ መደበኛው ልብሱ ባይለውጥ ኖሮ አይያዝም ነበር። ልብሱን በሚቀይርበት ወቅት የአውሮፕላኑ አስተናጋጆች ማያታቸውን ተከትሎም ነው የተያዘው።

የኢድ አል አድሃ በዓል ምክንያት በማድረግ አብዛኛዎቹ አየር መንገዶች ጉዞን ገድበዋል።

ፖሊስ ለጋዜጠኞች እንደተናገረው ሰውየው አውሮፕላኑ ከወረደ በኋላ በቁጥጥር ስር መዋሉን እና ወዲያውኑም የኮቪድ-19 ምርመራ እንደተደረገለት ነው።

የኮሮናቫይረስ እንዳለበት ሲታወቅም ቤቱ እንዲቆይና ራሱንም እንዲያገል ተነግሮታል።

የአስራ አራት ቀኑ ለይቶ ማቆያ ካለቀ በኋላ አቃቤ ህግ ክስ እንደሚመሰርት አስታውቋል።

በእስያ የቫይረሱ ማዕከል በሆነችው ኢንዶኔዥያ ውስጥ የጉዞ ገደቦች ጥብቅ ሆነዋል።

የደቡብ ምስራቋ እስያዋ ሃገር ኢንዶኔዥያ በየቀኑ 50 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ይያዛሉ።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ሆስፒታሎች በታካሚዎች መበራከት እና ኦክስጅንን ጨምሮ በሌሎች ህክምና ቁሳቁሶች እጥረትም ሃገሪቷ ችግር ውስጥ ገብታለች ተብሏል።

የኮሮናቫይረስ ከተከሰተበት እለት ጀምሮ ሶስት ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 72 ሺህ ግለሰቦችም ህይወታቸውን አጥተዋል።

ዘገምተኛ የክትባት አስራርና ዴልታ የተባለው በከፍተኛ ፍጥነት የሚተላለፈው የኮሮናቫይረስ አይነት ለአዳዲስ ተጠቂዎች መበራከት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ተጠቅሷል።