ኢትዮጵያ የግብጽ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን ውድቅ አደረገች

ዲና ሙፍቲ

የግብጽ መገናኛ ብዙኃን የሕዳሴ ግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትን በተመለከተ ሲያሰራጩ የነበረውን ዘገባ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር አጣጣለ።

ከሰሞኑ በርካታ የግብጽ መገናኛ ብዙኃን "ኢትዮጵያ ያቀደችውን ያህል ውሃ ማከማቸት አልቻለችም" የሚሉ ዘገባዎችን ሲያሰራጩ ነበር።

ከመገናኛ ብዙኃኖቹ መካከል 'ኢጂፕት ኢንዲፔንደት' የተሰኘው የኢትዮጵያ የውሃ፣ ኢነርጂ እና መስኖ ሚንስቴር የግድቡ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል ያለው "ሐሰት ነው" የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር።

የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ 'ኢትዮጵያ የፈለገችውን ያህል ውሃ አላከማቸችም' የሚለው ዘገባ የሐሰት ነው ብለዋል። አምባሳደሩ ከዚህ ቀደምም ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ስታስጀምር ግንባታው የሐሰት ነው የሚሉ አንዳንድ አካላት ነበሩ ሲሉ አክለዋል።

ግድቡ በአሁኑ ወቅት ምን ያህል የውሃ መጠን ይዞ እንደሆነ የተጠየቁት አምባሳደር ዲና፤ የውሃ መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ እንደማያውቁ እና ጉዳዩን የሚያውቁት የውሃ ባለሙያዎች እንደሆኑ ተናግረዋል።

"ግድቡን እየገነቡ ያሉ ሰዎች እንደነገሩን ከሆነ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እንደተጠናቀቀ እና በቅርቡ ሁለት ተርባይነሮች ሥራ እንደሚጀምሩ ነው" ብለዋል አምባሳደር ዲና።

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድቡን ግንባታ እየቀጠለች በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ወደሚደረገው ድርድር ለመመለስ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

የሳዑዲ ተመላሽ ዜጎች

አምባሳደር ዲና የኢትዮጵያ መንግሥት ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የነበሩ ከ41 ሺህ በላይ ሰዎችን ወደ አገር መመለሱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በሳዑዲ ለችግር የተጋለጡ ዜጎቿን በፍጥነት ወደ አገር ለመመለስ የአጭር ጊዜ ዝግጅት ያደረገችው ከሶስት ሳምንት በፊት ነበር።

እስካሁን ከ41 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ አገር ቤት ለመመለስ 130 በረራዎች መከናወናቸውን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቱ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, MoFA Ethiopia/Facebook

መንግሥት ቀደም ሲል 40 ሺህ ዜጎችን ወደ አገር ቤት ለመመለስ እቅድ ቢኖረውም ዜጎችን የማፈናቀሉ እና ለችግር የመዳረጉ ተግባር በመጨመሩ ወደ አገር የሚመለሱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን አምባሳደሩ ተናግረዋል።

"የሳዑዲ መንግሥት በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ስቃይ እንዲያቆም በዲፕሎማሲውም ሥራዎች እየተከናወኑ ነው" ብለዋል።

በሌላ በኩል በደቡብ አፍሪካ በተከሰተው ብጥብጥ ንብረት የወደመባቸው እና ንብረት የተዘረፈባቸው ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ተናግረው ጉዳት የደረሰባቸው የሕክምና እርዳታ እያገኙ ነው ብለዋል።

ከሰሞኑ በተቀሰቀሰው የደቡብ አፍሪካው ብጥብጥ ሕይወቱ ያለፈ ዜጋ አለመኖሩን ያረጋገጡት አምባሳደር ዲና፤ የዜጎችን ጉዳይ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በቅርበት እየተከታተለ ነው ብለዋል።