በኦሊምፒክ መድረክ ኢትዮጵያን በቴኳንዶ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚወክለው ወጣት

የ23 ዓመት ወጣት የሆነው ሰለሞን ቱፋ የቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ በቴኩዋንዶ መድረክ ይወክላል።

የፎቶው ባለመብት, Solomon Tufa/Facebook

የምስሉ መግለጫ,

የ23 ዓመት ወጣት የሆነው ሰለሞን ቱፋ የቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ በቴኩዋንዶ መድረክ ይወክላል።

አትሌት ሰለሞን ቱፋ ዛሬ በሚጀመረው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ በቴኳንዶ ስፖርት መድረክ ይወክላል።

የቴኳንዶ ውድድር ከአውሮፓውያኑ 2000 ጀምሮ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ መካተት የጀመረ ሲሆን የ23 ዓመቱ ወጣት ሰለሞን በዚህ ውድድር ለአገሩ ጥሩ ውጤትን ለማምጣት ማቀዱን ይናገራል።

ሰለሞን በቶኪዮ ኦሊምፒክ መሳተፍ የቻለው እአአ 2020 በአፍሪካ ደረጃ ሞሮኮ ላይ በተካሄደው ውድድር ስኬታማ መሆኑን ተከትሎ እንደሆነ ያስረዳል።

በኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ መሳተፍ "የረዥም ጊዜ ህልሜ ነበር" የሚለው ሰለሞን፤ ይህን ህልሙን ለማሳካት ትምህርቱን ከማቋረጥ ጀምሮ ብዙ እልህ አስጨራሽ ጥረቶችን ማድረጉን ያስረዳል።

"በዚህ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ብዙ ውድድሮችን ማድረግ ነበረብኝ፤ ከአገር ውጪ ብዙ ውድድሮችን አሸንፊያለሁ። ጉዳት ሁሉ አጋጥሞኝ እዚህ ደርሻለሁ" ይላል።

"የሚቻለኝን ሁሉ አድርጌያለሁ። ፈጠሪ ከረዳኝ የሜዳሊያ ዝርዝር ውስጥ ገብቼ የአገሬን ሰንደ ዓላማ ማንሳት እፈልጋለሁ" በማለት ሰለሞን ከቢቢሲ ተናግሯል።

ቴኳንዶ (Taekwondo) የኮሪያ ማርሻል አርት ሲሆን እጅ እና እግርን መጠቀምን ይጠይቃል።

  • Tae = ማለት በእጅ መማታት
  • Kwon = በእግር መማታት ማለት ሲሆን
  • Do = ማለት ደግሞ አርት ወይም ስልት እንደማለት ነው።

ሰለሞን በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከ58 ኪሎ ግራም በታች በሚባለው ምድብ ውስጥ የሚወዳደር ይሆናል። በዚህ የውድድር መስክ 16 ስፖርተኞች ይወዳደራሉ።

"ውድድሩ በአንድ ቀን ነው የሚጠናቀቅ ነው። ጠዋት ጀምሮ እስከ ምሽት ሊዘልቅ ይችላል። አንድ ዙር ካሸነፍክ ወደ ቀጣይ ዙር እያለፍ ትሄዳለህ።"

የኦሊምፒክ ውድድር እንደመሆኑ መጠን ሁሉም አትሌት ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ እንደሚቀርብ የሚናገረው ሰለሞን፤ "ተዘጋጅቻለሁ ምንም የምፈራው ነበር የለም" በማለት ይናገራል።

ባለፉት ስምንት ወራት በሳምንት ስድስት ቀናት ጠዋት እና ማታ በየቀኑ ከ5 አስከ 6 ሰዓታት ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን የሚያስረዳው ሰለሞን ያለፈውን አንድ ወር ደግሞ ወደ ጀርመን አገር በመሄድ የመጨረሻ ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበረ ይናገራል።

ሰለሞን ውድድሩን ቅዳሜ ሐምሌ 17/2013 ዓ.ም ያደርጋል።

ሰለሞን ቱፋ ማነው?

ትውልዱ አርሲ በቆጂ ቢሆንም እድገቱ ግን አዲስ አበባ ከተማ ነው።

መስታወት ቱፋ እና ትዕግስት ቱፋ የተባሉት ሁለት እህቶቹ በማራቶን ውድድር ይታወቃሉ።

የፎቶው ባለመብት, Solomon Tufa/ Facebook

"ከእኛ ቤተሰብ ሦስት ሰው በኦሊምፒክ ተሳትፏል። ቤተሰቦቼ ይህን ሲያስቡ በጣም ደስ ይላቸዋል" በማለት ከዚህ በፊት ሁለት እህቶቹ በኦሊምፒክ መወዳደራቸውን ያስታውሳል።

ከሩጫው ይልቅ ወደ ቴኳንዶ ውድድር ፍላጎት ያደረበት፤ ታላቅ ውንድሙ ይህን ስፖርት ሲሰራ ከተመለከተ በኋላ በቴክዋንዶ ስፖርት ፍቅር መውደቁን ይናገራል።

ሰለሞን እስካሁን በበርካታ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ የተለያዩ ውጤቶችን ቢያስመዘግብም ሞሮኮ ላይ ተወዳድሮ ያመጣው ውጤት ግን "ትልቁ ስኬቴ ነው" ይላል። እ

አአ 2018 ላይ በሞሮኮ ተካሂዶ በነበረው የአፍሪካ ቴኳንዶ ሻምፒዮን በ54 ኪሎ ግራም ምድብ የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፉን ይናገራል።

ዎርልድ ቴንዶ ፕሬዝደንትስ ካፕ በተባለ ውድድር ላይ የወርቅ ተሸላሚ በመሆኑ 'ምርጡ የአፍሪካ አትሌት' ተብሎ መሸለሙን ሰለሞን ለቢቢሲ ተናግሯል።