ጂንስ በመልበሷ በቤተሰቧ አባላት የተገደለችው ሕንዳዊት

ኔሃ ፓስዋን

የፎቶው ባለመብት, Rajesh arya

የምስሉ መግለጫ,

ጅንስ በመልበሷ የተገደለችው ኔሃ ፓስዋን

በቅርቡ ሴቶችና ታዳጊዎች በቤተሰቦቻቸው አማካኝነት በጭካኔ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው የሚገልጹ ዘገባዎች በሕንድ ውስጥ በርክተዋል።

እነዚህ ክስተቶች ምን ያህል ታዳጊዎችና ሴቶች በቤታቸውም ቢሆን ደኅንነታቸው ያልተጠበቀ መሆኑን ማሳያ ነው በሚልም ትኩረት ስቧል።

ባለፈው ሳምንት በሰሜናዊው የኡታር ፕራዴሽ ግዛት የ17 ዓመቷ ኔሃ ፓስዋን ጂንስ በመልበሷ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ ድብደባ ተፈፅሞባት ህይወቷ አልፏል።

እናቷ ሻኩንታላ ዴቪ ፓስዋን ለቢቢሲ ሂንዲ እንደተናገረችው ከአለባበሷ ጋር በተገናኘ ከአያቷና ከአጎቷ ጋር ከፍተኛ ክርክር ውስጥ ገብታ የነበረ ሲሆን በምላሹም ክፉኛ ደብድበዋት ህይወቷ አልፏል።

"ሙሉ ቀን ፆማ ነበር። ምሽት ላይ ጂንስና ከላይ ቲሸርት ለብሳ የአምልኮ ሥርዓቷን አከናወነች። አያቶቿ ኦለባበሷን አልወደዱትም ነበርና ተቃወሟት። ኔሃም ጂንስ መልበስ ምንም ማለት አይደለም እለብሳለሁ አለቻቸው" ትላለች።

ክርክራቸው እየጦፈ መጣና መጨረሻም ወደ ድብደባ እንደተቀየረ ትናገራለች።

ሻኩንታላ እንደምትለው ልጇ ራሷን ስታ ከወደቀች በኋላ የአባቷ ቤተሰቦች ባጃጅ ጠርተው ወደ ሆስፒታል ወሰዷት።

"አብሬያቸው እንድሄድ አልፈቀዱልኝም። እናም ለራሴ ዘመዶች ነግሬያቸው ወደ ሆስፒታል ሊፈልጓት ቢሄዱም ሊያገኟት አልቻሉም" ትላለች።

በነገታውም ሻኩንታላ እንደምትለው በክልሉ ውስጥ በሚፈሰው የጋንዳክ ወንዝ ላይ ከሚገኘው ድልድይ ላይ የአንዲት ልጃገረድ አስከሬን ተንጠልጥሎ እንደነበር ሰማች። ለማጣራት ሲሄዱ የኔሃ አስከሬን ሆኖ አገኙት።

የኔሃ አያቶች፣ አጎቶች፣ አክስቶች፣ የአጎት ልጆች እና የባጃጅ ሹፌሩን ጨምሮ በ10 ሰዎች ላይ ፖሊስ የግድያ እና ማስረጃን በማጥፋት ወንጀል ክስ አቅርቧል። ተከሳሾቹ እስካሁን ይፋዊ መግለጫ አልሰጡም።

የፎቶው ባለመብት, Rajesh arya

የምስሉ መግለጫ,

የኔሃ እናት ሻኩንታላ ዴቪ

የፖሊስ ከፍተኛ ኃላፊ ሽሪያስ ትሪቲ ለቢቢሲ ሂንዲ እንደተናገሩት የሟቿ አያቶች፣ አጎት እና የባጃጁን ሾፌር ጨምሮ አራት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ ነው።

ፖሊስ ተጨማሪ ተጠርታሪዎችን በመፈለግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የኔሃ አባት አማርናት ፓስዋን በፑንጃብ ግዛት በግንባታው ዘርፍ በቀን ሠራተኝነት የሚተዳደሩ ሲሆን የልጃቸው ሃዘን ልባቸውን እንደሰበረውና ያለቻቸውን ቤሳ ቤስቲን ሰባስበው ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለማስተማር እንዴት እንደለፉም ተናገግረዋል።

ሻኩንታላ ዴቪ በበኩሏ ኔሃ ፖሊስ የመሆን ህልም እንደነበራት ገልፀው ነገር ግን "አሁን ህልሟ መቼም እውን አይሆንም" ብላለች።

የኔሃ እናት እንደምትለው ልጃቸው ትምህርቷን እንድታቋርጥ የአባቷ ቤተሰቦች ጫና እያደረጉባት የነበረ መሆኑን ገልፃ አብዛኛውን ጊዜ ከባህላዊ የሕንድ አልባሳት ውጪ ሌላ ማንኛውንም ነገር ከለበሰች ያዋርዷትና ይሰድቧት ነበር።

ኒሃ ዘመናዊ ልብሶችን መልበስ፣ መዘነጥ ትወድ ነበር። ቤተሰቦቿ ለቢቢሲ ካጋሯቸው ሁለት ፎቶግራፎች መካከል አንዱ ረዥም ቀሚስ የለበሰች ሲሆን በአንደኛው ደግሞ ጂንስ ሱሪና ጂንስ ጃኬት ለብሳ ትታያለች።

በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት በአባታዊ (ፓትሪያርኪ) ሥርዓት ምክንያት በሴቶች እና ታዳጊዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ከፍተኛ ሲሆን ይህንንም በዋነኝነት የሚያደርጉት የቤተሰቦች ታላላቅ አባላት ናቸው።

በሕንድ ውስጥ ሴት ልጆች ገና ከመወለዳቸው በፊት የመገደል አደጋ ይጋረጥባቸዋል።

በርካታ ቤተሰቦች ወንድ ልጅ መውለድ ስለሚፈልጉ ሴቶችን በሚወልዱበት ወቅት የሚገድሉበት አጋጣሚ በርካታ ነው።

የቤት ውስጥ ጥቃት ብሎም ግድያ በአገሪቱ ውስጥ ተንሰራፍቶ ይገኛል። ለምሳሌም ያህል ሴቶች በቂ ጥሎሽ ባለመክፈል በአማካኝ በየቀኑ 20 ሴቶች ይገደላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በትናንሽ ከተሞች እና በሕንድ የገጠር አካባቢዎች ውስጥ ያሉ ሴቶች እና ታዳጊዎች በአካባቢ አመራሮች እንዲሁም ቤተሰባቸው ውስጥ ባሉ አባወራዎች ከፍተኛ ክልከላና ቅጣት ይደርስባቸዋል።

አብዛኛውን ጊዜ የሚለብሱትን፣ የሚሄዱበትን ቦታ ወይም በምን መንገድ መናገር እንዳለባቸው ጥብቅ ትዕዛዝ የሚሰጣቸው ሲሆን ትንሽ ጥፋት ተብሎ የሚቆጠር ነገር ከተገኘባቸውም ይቀጣሉ።

በቤተሰቦቻቸው አባላት በሴት ልጆች እና ታዳጊዎች ላይ ከተዘገቡ በርካታ የጭካኔ ጥቃቶች መካከል በቅርቡ ሕንዳውያንን ያስደነገጠው የኔሃ በአለባበስ ምርጫዋ ሳቢያ የተፈጸመባት ጥቃትና ግድያ ከብዙዎቹ አንዱ ነው።

ባለፈው ወር በአጎራባቿ ግዛት ማድያ ፕራዴሽ አሊራጅፑር ወረዳ አንዲት የ20 ዓመት ወጣት ሴት በአባቷና በሦስት የአጎቷ ወንድ ልጆች ስትደበደብ የሚያሳይ ቪዲዮ በርካቶችን አስደንግጧል።

በርካቶች ቁጣቸውን ማሰማታቸውን ተከትሎም ፖሊሶች በግለሰቦቹ ላይ ክስ የከፈተ ሲሆን የደበደቧት የቤተሰብ አባላት ጥቃት ከሚያደርስባት ባሏ በመሸሿ እየቀጣናት ነው ብለዋል።

ይህ ድርጊት ከመከሰቱ ከአንድ ሳምንት በፊት ሪፖርቶች እንዳመለከቱት ሁለት ሴት ልጆች ደሃ በምትባል በአጎራባች በምትገኝ ወረዳ ውስጥ ከአንድ ወንድ የአጎት ልጃቸው ጋር በስልክ በመነጋገራቸው ያለምንም ርህራሄ በቤተሰቦቻቸው መደብደደባቸው ተነግሯል።

የክስተቱ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት አንዷ ልጅ በፀጉሯ መሬት ላይ ስትጎተት፣ በእንጨትና በዱላ ስትደበደብ ነው።

ድብደባውንም የሚፈፅሙት ወላጆቿ፣ የአጎቷ ልጆችና ወንድሞቿ ናቸው። ቪዲዮው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መውጣቱን ተከትሎ ፖሊስ ሰባት ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።

በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲሁ ባለፈው ወርም በጉጅራት ግዛት ሁለት ታዳጊዎች በሞባይል ስልኮቻቸው በማውራታቸው ዘመዶቻቸውን ጨምሮ ቢያንስ 15 ወንዶች እንደበደቧቸው ፖሊስ አስታውቋል።

የሥርዓተ-ፆታ ተሟጋች የሆኑት ሮሊ ሺቭሃር "በ21ኛው ክፍለ ዘመን ልጃገረዶችን ጂንስ ስለለበሱ ወይም በሞባይል ስልክ ስላወሩ መደብደባችንና መግደላችን አስደንጋጭ ነው" ብለዋል።

አባታዊ ሥርዓት "በህንድ ውስጥ ካሉ ታላላቅ ችግሮች መካከል አንዱ ነው" የሚሉት ተሟጋቿ ፖለቲከኞች፣ መሪዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ብዙውን ጊዜ መጥፎ ምሳሌ የሚሆኑና ፆተኛ አስተያየቶችን የሚሰነዝሩ ሲሆን፤ የጾታ እኩልነት መልዕክትም ለማኅበረሰቡ እና ለቤተሰብ እንደማይደርስ ጠቁመዋል።፡

ተሟጋቿ እንደሚሉት "መንግሥት ለሴት ልጆች ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው በማለት ለደኅንነታቸው ታላቅ እቅዶችን ያውጃል ነገር ግን በመሬት ላይ ምንም የሚከሰት ነገር የለም" ብለዋል።

በምዕራቡ ዓለም በቤታቸው ውስጥ ለአደጋ የተጋለጡ ልጆች ወይም ሴቶች ወደ መጠለያ ሊወሰዱ ወይም ወደተለያዩ ማዕከላት ሊገቡ ይችላሉ።

"በሕንድ ውስጥ ያሉት የመጠለያ ቤቶች እና ማዕከላት ጥቂቶች ናቸው እና አብዛኛዎቹ በመጥፎ ሁኔታ የተያዙ በመሆናቸው ማንም ሰው እዚያ ለመኖር አይፈልግም። መንግሥታችን ተጨማሪ ገንዘብ በመመደብ ሁኔታቸውን ማሻሻል አለበት" ሲሉ ተሟጋቿ ተናግረዋል።

"ነገር ግን ብቸኛው የረጅም ጊዜ መፍትሔ ሴት ልጆች መብቶቻቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ነው" በማለት አፅንኦት ይሰጣሉ።