በአፋርና በሶማሌ አዋሳኝ የተከሰተው ግጭት የሚያስከትለው ጉዳት እንዳሳሰበው ኢሰመኮ ገለጸ

የኢሰመኮ አርማ

የፎቶው ባለመብት, EHRC

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአፋርና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከአንድ ሳምንት በፊት የተከሰተው ግጭት እያስከተለ ያለው ጉዳት እንዳሳሰበው ገለጸ።

ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ በገዳማይቱ ከተማ ከሐምሌ 17/2013 ዓ. ም ጀምሮ የተከሰተ ነው ያለው ግጭት በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የሕይወት መጥፋት፣ የንብረት መውደምና መፈናቀልን እያስከተለ መሆኑ አሳስቦኛል ብሏል።

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ሁለቱ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በማንሳት በሚወዛገቡበት ስፍራ በተከሰተ ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን የሶማሌ ክልል ባለሥልጣናት ገልጸው ነበር።

የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ሮብሌ፤ በገዳማይቱ ከተማ በተከሰተው ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። ነገር ግን ይህንን አሃዝ ከሌላ ወገን ለማረጋገጥ አልተቻለም።

ስማቸው ያልተጠቀሰ ሁለት የሶማሌ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በግጭቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው መግለጫ፤ በግጭቱ ምክንያት በሰው ላይ የደረሰውን ሞትና ጉዳት እንዲሁም በንብረት ላይ ያጋጠመውን የውድመት መጠን ለማወቅ የመረጃ ውስንንት እንዳለ አመልክቷል።

ጨምሮም በግጭቱ ቦታዎች እና በአዋሳኝ ከተሞች ያለው የጸጥታ ሁኔታ ወደነበረበት ባለመመለሱና የተወሰኑ መንገዶች በመዘጋታቸው መደበኛ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸውን አመልክቷል።

በግጭቱ ሳቢያ ከጂቡቲ ወደ አዲስ አበባ የሚወስዱት የባበቡርና የተሽከርካሪዎች መንገዶች ተዘግተው እንቅስቃሴ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፤ ከጥቂት ቀናት በኋላ የአገር ሽማግሌዎችና የክልሉ ባለሥልጣናት ባደረጉት ጥረት መንገዶቹ እንዲከፈቱ መደረጋቸው ተገልጿል።

ሁለቱን ክልሎች በሚያዋስኑ አካባቢዎች በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ላይ በሚነሱ የይገባኛል ጥያቄዎች ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ግጭቶች ያጋጠሙ ሲሆን በሰውና በንብረት ላይ ከዚህ ቀደምም ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።

ባለፈው ሳምንት በተከሰተው ግጭት ከአካባቢው ተፈናቅለው ወደ ሙሊ ከተማና ወደ ሌሎች ቀበሌዎች በመሄድ ተጠልለው ለሚገኙ ነዋሪዎች የሰብዓዊ እርዳታ በአፋጣኝ ለማቅረብ እንቅስቃሴ እንደተደረገና አቅርቦቱ እንዳይስተጓጎል የጸጥታ አካላት ጥበቃ ማድረግ ቀዳሚ እርምጃቸው ሊሆን እንደሚገባ ኢሰመኮ አሳስቧል።

ጨምሮም በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ግጭት ለመፍታት በፌደራል መንግሥት እንዲሁም በአፋርና በሶማሌ ክልሎች በኩል ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብሏል።