ከአቶ ጌታቸው ረዳ ጋር የታዩት የተመድ ሠራተኛ ወደ ሌላ አገር ተዘዋወሩ

አቶ ጌታቸው ረዳ እና ቶሚ ቶምሰን

የፎቶው ባለመብት, Social media

የፌደራሉ መንግሥት በሽብርተኛነት ከሰየመው የህወሓት ከፍተኛ አመራር ጋር የታዩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሠራተኛ ወደ ሌላ አገር መዘዋወራቸው ተገለጸ።

ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መቀለን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ የህወሓት ኃይሎች ከተማዋን ከተቆጣጠሩ በኋላ በሳተላይት ስልክ እያወሩ ከሚታዩት ከአቶ ጌታቸው ረዳ ጋር አንድ የውጭ አገር ዜጋን የሚያሳይ ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መሰራጨቱን ተከትሎ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

በፎቶው ላይ የሚታየት ግለሰብ በተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የአደጋ ጊዜ አስተባባሪ የሆኑት ቶሚ ቶምሰን ናቸው።

ከፎቶው ጋር በተያያዘ በርካታ ማብራሪያዎችና መላምቶች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲዘዋወሩ የቆዩ ሲሆን ቢቢሲ ጉዳዩን በሚመለከት ከተቋሙ ማብራሪያ ጠይቆ ነበር።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ በሰጠው ምላሽ በፎቶው ላይ የሚታዩት የድርጅቱ ሠራተኛ ቶማስ ቶምሰን ከኢትዮጵያ ተቀይረው ወደ ሌላ አገር ሄደዋል።

"ግለሰቡ ከኢትዮጵያ የወጡበትን ምክንያት በተመለከተ የተዛቡ መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲዘዋወሩ እንደነበር ተረድተናል። እነዚህ ሪፖርቶች መሠረተ ቢስ ናቸው" ሲል ድርጅቱ ለቢቢሲ በላከው የኢሜይል ምላሽ ገልጿል።

ግለሰቡ ከአገር የወጡት በተለመደው የድርጅቱ የሠራተኞች ዝውውር ሂደት መሠረት እንደሆነ እና ወደፊት እንደሚመለሱም ጨምሮ ገልጿል።

ቢቢሲ ግለሰቡ ስለታዩበት ፎቶና በምን አጋጣሚ ከአቶ ጌታቸው ጋር እንደተገናኙ ለዓለም ምግብ ፕሮግራም ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።

የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያለው ነገር የለም። ቢቢሲም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም።

ግለሰቡ ቶሚ ቶምሰን የተቋሙ የአደጋ ጊዜ አስተባባሪ የነበሩ ሲሆን፤ በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ቀውስ ተከትሎም በክልሉ ውስጥ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሚያካሂዳቸውን የአደጋ ጊዜ ተግባራት ሲያስተባብሩ ቆይተዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል ውስጥና በሌሎችም የአገሪቱ አካባቢዎች የተለያዩ የሰብዓዊ ድጋፎችን የሚያቀርብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ አካል ነው።

የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ካስወጣ በኋላ የህወሓት ኃይሎች በአዋሳኝ የአማራና የአፋር ክልል ጥቃት በመሰንዘራቸው በተከሰተ የደኅንነት ስጋት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ወደ ትግራይ የሚያጓጉዘው የእርዳታ አቅርቦት ተቋርጦ እንደነበር ይታወሳል።

ነገር ግን በዚህ ሳምንት ከአፋር፣ ሰመራ ወደ ትግራይ፣ መቀለ የሚያደርገውን የእርዳታ አቅርቦት መልሶ በመጀመር ከሁለት መቶ በላይ ተሽከርካሪዎች ጉዞ መጀመራቸውን ድርጅቱ ለቢቢሲ ገልጿል።