ታሊባን ሶስት ቁልፍ ከተሞችን መክበቡን ተከትሎ ውጊያው መፋፋሙ ተነገረ

የአፍጋኒስታን ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, EPA

በደቡባዊና ምዕራብ አፍጋኒስታን በሚገኙ ሶስት ዋና ዋና ከተሞች ዙሪያ ውጊያው መፋፋሙ ተነግሯል።

የታሊባን ታጣቂዎች እነዚህን ከተሞችም ለመቆጣጠር ከአፍጋኒስታን መንግሥት ኃይሎች ጋር እየተፋለሙ ነው።

የታሊባን ተዋጊዎች በተወሰነው ሄራት ፣ ላሽካር ጋህ እና ካንዳሃር ክፍሎች ገብተዋል።

በአፍጋኒስታን የነበሩት የውጭ አገር ወታደሮች ሙሉ በሙሉ በመስከረም ወር ይወጣሉ መባላቸውን ተከትሎም የታሊባን ጦር በርካታ የገጠር ግዛቶችን ተቆጣጥሯል።

የታሊባን ዋነኛ ትኩረት ከተሞችን መቆጣጠር ሆኗል።

ነገር ግን አሁንም የነዚህ ቁልፍ ከተሞች እጣ ፈንታ አልታወቀም። የመንግሥት ኃይሎችም ምን ያህል የታሊባንን ጦርስ ተቋቁመው መቆየት ይችላሉ የሚል ጥያቄም ተፈጥሯል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የሰብዓዊ ቀውሱም ሁኔታ የከፋ ይሆናል የሚል ፍራቻም ነግሷል።

በአሁኑ ወቅት ታሊባን ግማሹን የአፍጋኒስታን ግዛት ተቆጣጥሮ የሚገኝ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በኢራንና በፓኪስታን የሚገኘው የድንበር መሸጋገሪያ ይገኝበታል።

በላሽካር ጋህ ፣ የታሊባን ታጣቂዎች በትናንትናው ዕለት ከግዛቱ አስተዳዳሪ ፅህፈት ቤት በጥቂት መቶ ሜትሮች ርቀት ብቻ የነበሩ ሲሆን ነገር ግን ከሌሊት በኋላ ተገፍተዋል ተብሏል።

በብዙ ቀናት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሙከራ ሲያደርጉ ለሁለተኛ ጊዜ ነበር። የአፍጋኒስታን ኃይሎች አዛዥ አርብ ዕለት በታጣቂዎቹ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ተናግረዋል።

ሁኔታው ተለዋዋጭ ቢመስልም ነገር ግን ብዙ የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ወታደሮች ህይወታቸውን ያጡበት የሄልማን ግዛት ዋና ከተማ ላሽካር ጋህ አሁን በጣም ተጋላጭ ይመስላል። የታሊባን ደጋፊ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆች የታጋዮቻቸውን ቪዲዮዎች በከተማው እምብርት ላይ ያደረጉትን ፍልሚያ እያሳዩም ነው።

የአፍጋኒስታን ልዩ ሀይሎች ታጣቂዎችን ወደ ኋላ እንዲገፉ ለመርዳት እየተላኩ ቢሆንም አንድ የአከባቢ ነዋሪ እንዳሉት ይህ ቢከሰት እንኳን የታሊባን በከፍተኛ ሁኔታ ግዛቶችን መቆጣጠርና ያለውን ጥንካሬ ማሳያ ስለሆነ ነገሮች ቀላል አይሆኑም።

ታጣቂዎቹ በተራ ቤተሰቦች ቤት ውስጥ ሰፍረው እንደሚገኙ የተገለፀ ሲሆን ይህም ውጊያውን ፈታኝ ያደርገዋል።

የበለጠ ረዥም እና ደም አፋሳሽ ውጊያ ወደፊት የሚጠብቅ ይመስላል።